የትግራይ ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም እና ሰላም እውን ሊሆን የሚችለው በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ መሆኑን ጋዜጠኛ ዳሞራ ያህያ ተናግሯል።
ጋዜጠኛው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት እና በተለያዩ ከተሞች እየተተገበሩ የሚገኙት የኮሪደር ልማቶች፣ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሲሠሩ የሚያመጡትን የላቀ ለውጥ እንደሚያሳዩ ገልጿል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በብሪክስ መድረክ ያስመዘገበችው ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ለቀጣይ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስረድቷል።
በትግራይ ክልል ሚዲያዎች ለረጅም ዓመታት በጋዜጠኝነት ያገለገለው ዳሞራ ያህያ፣ አሁን ላይ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በነፃነት በሙያው እየሠራ እንደሚገኝ አብራርቷል።
በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የህወሓት ቡድን የሻዕቢያ ታዛዥ በመሆን የትግራይን ሕዝብ ለአደጋ እያጋለጠው መሆኑንም ጠቁሟል።
"በትግራይ ክልል ኢትዮጵያዊ አቋም መያዝ እንደ ወንጀል የሚቆጠር በመሆኑ በክልሉ የሚፈጸሙ በደሎችን እና እውነታዎችን በይፋ መናገር አይቻልም" የሚለው ጋዜጠኛው፣ ይህ አፈና ህሊና ያላቸው ምሁራንና ጋዜጠኞች በነፃነት እንዳይሠሩ ከማድረጉም ባለፈ ብዙዎችን ለስደት መዳረጉን አስታውቋል።
የህወሓት ቡድን የትግራይን ሕዝብ በታጋችነት በመጠቀም የራሱን የፖለቲካ ቁማር እንደሚጫወት እና በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ሴራ እየሸረበ መሆኑን ጋዜጠኛው አስገንዝቧል።
ይህም አካሄድ ሕዝቡን ከሰላም፣ ከልማት እና ከመደበኛ የኑሮ ዘይቤ የሚያርቅ መሆኑን አክሎ ገልጿል።
የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላምን እና ልማትን እንጂ የቡድኖችን የፖለቲካ ሴራ አለመሆኑን የጠቆመው ጋዜጠኛ ዳሞራ ያህያ፣ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት ሕዝቡን ወደ ትክክለኛው የኢትዮጵያዊነት ጎዳና እንዲመልሱ ጥሪ አቅርቧል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: