“ዳገታ” በወላይታ ባህላዊ ሥርዓት ውስጥ ሁለት ሰዎችን “ከወንድማማችነት በላይ” በሆነ ፍጹም ታማኝነት ስና ፍቅር የሚያስተሳስር፣ እስከ ዕለተ ሞት የሚዘልቅ የማይፈርስ የፍቅር እና የአብሮነት ቃል-ኪዳን ነው።
በጊፋታ በዓል ወቅት ሁለት ሰዎች በጋራ በመሆን የጊፋታ ልዩ ባህላዊ መጠጥ የሆነውን “ቦርዴ” በአንድ ቅል ይጋራሉ።
በመካከላቸው ያለውን ወዳጅነት ወደ ላቀ ታማኝነት ለማሸጋገር ሲሉ “ኑና ሻኮፖ፣ ቆሮፖ” (አይለየን፣ እንዋደድ፣ እንጠባበቅ) በሚል ቃል-ኪዳን መጠጡን አብረው ይጎነጫሉ።
ይህ በአንድ ቅል መጋራት የሚከናወን ሥርዓት “ከእንግዲህ እኛ ሁለት አካል አይደለንም፤ ሀሳባችን፣ መንፈሳችን እና ሕይወታችን አንድ ሆኗል” የሚል ማረጋገጫ ሲሆን፣ በማኅበረሰቡ ፊት የሚፈጸም ይፋዊ የስምምነት ማኅተምም ጭምር ነው።
ዳገታ የፈፀሙ ወዳጆች እርስ በርስ “ኔጌ ታጋ፣ ታጌ ኔጋ” (የእኔው የአንተ ነው፣ የአንተም የእኔ ነው) ይባባላሉ።
ይህ እንዲሁ በቃል ብቻ የሚነገር ሳይሆን በተግባር የሚገለጥ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ዋስትና መገለጫ ነው።
የአንዱ መሬት፣ ከብት ወይም ጥሪት የሌላውም ጭምር በመሆኑ፣ አንዱ ችግር ላይ ሲወድቅ ሌላው ያለ ምንም ማቅማማት ሀብቱን ያካፍላል።
ይቅርታ እና ራስን በራስ የማከም ጥበብ “ዳገታ” የፈጸሙ ወገኖች የሚተገብሩት የዕለት ተዕለት የሕይወት አካል ነው።
በሰው ልጅ ተፈጥሮ አለመግባባቶች እና ቅሬታዎች መፈጠራቸው የማይቀር ቢሆንም፣ የዳገታ ትስስር ግን ለየት ያለ የችግር አፈታት ጥበብ አለው።
በመካከላቸው ፀብ ወይም ቅሬታ ቢፈጠር እንኳ “አፉላ ግዶን ውርሶስ” (በመሐላችን ሰው አይግባ፤ ጉዳዩ በይቅርታ ይለቅ) ተባብለው ራሳቸው ይቅር ይባባላሉ።
የዳገታ ባለአደራዎች በመካከላቸው ላለ ጠብ ዳኛ ወይም ሦስተኛ ሰው አይጠሩም፤ ቂማቸውን ራሳቸው በፍቅር እና በይቅርታ አጥበው ያጸዱታል።
ይህ እስከ ዕለተ ሞት የሚዘልቅ ጥልቅ የፍቅር መሐላ እና የዳገታ ማሰሪያ፣ አንዱ ሲደሰት አብሮ የመደሰት፣ እንዲሁም አደጋ ሲደርስበት ጉዳቱን እንደ ራሱ የሚቆጥርበት እውነተኛ የሰውነት መገለጫ ነው።
ይህ ትስስር የሚጸናው እስከ መቃብር ድረስ በመሆኑ አንዱ ቢሞት እንኳ የቀረው ወዳጅ የሟቹን ቤተሰብ እና ልጆች እንደ ራሱ አድርጎ የመንከባከብ ባህላዊና የሞራል ግዴታ አለበት።
የወላይታ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል የሆነው “ጊፋታ” እና አካል የሆነው “ዳገታ” በውስጣቸው የያዟቸው ጥልቅ ማኅበራዊ ፍልስፍናዎች፣ ሰብዓዊ እሴቶች እና ዘላቂ የሰላም እሳቤዎች ትውልድን ተሻግረው ከዓምና ጀምሮ በዩኔስኮ የማይዳሰስ የዓለም የሰው ዘር ወካይ ቅርስ ሆነው መመዝገባቸው ይታወሳል።
በሰብለወርቅ ኤልያስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: