የከምባታ ብሔር የዘመን መለወጫ ‘መሳላ’ በዓል ዋዜማ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።
በአካባቢው ባህል መሠረት ከእርድ ቀን አስቀድሞ የሚከበረው "የአተካና ምሽት" ወይም "የእናቶች መሳላ" በመባል የሚታወቀው የአተካና እራት የመብላት ሥነ-ሥርዓት በዱራሜ ከተማ፣ በኡቱቢ ወጋ አደባባይ እየተካሄደ ይገኛል።
አተካና የተመረጠ የቆጮ ዓይነት (ሜሬሮ) ከቅቤ፣ ከአይብ እና ከተለያዩ ቅመማ ቅመም ጋር በእናቶች በጥንቃቄና በብልሃት ተዋህዶ የሚዘጋጅ ምግብ ነው።
አተካና በባህላዊ መንገድ ተጠብቆ ከተቀመጠ ለረጅም ጊዜ ሳይበላሽ የሚቆይ ለሁሉም ሰው ተስማሚ የሆነ ምግብ ነው።
አተካና ሰዎች በዋናው ክብረ በዓል ወቅት ለሚመገቧቸው ሥጋ ነክ ምግቦች ሆድን አለስልሶ የማቆየት ፋይዳም እንዳለው ይገለፃል።
በዱራሜ እየተከበረ ያለው የአተካና ምሽትም ይህን ባህላዊ እሴት በማጉላት ትውልዱ ትውፊቱን እንዲያውቅ፣ እንዲጠብቅና በፍቅር ማዕድ በመጋራት አንድነቱን እንዲያጠናክር ለማስቻል ያለመ ነው።
በአያንቱ እምሩ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: