Search

ተመድ ሲፈተን፦ የኢትዮጵያ ፍትሐዊ የፖለቲካ ጥሪ፣ የማድረግ አቅም ልዕልና እና የዓለም አቀፍ ተፈላጊነት አዲስ ምዕራፍ

ማክሰኞ መስከረም 12, 2019 33

በኒውዮርክ በሚካሄደው የዓመቱ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የዓለም መሪዎች በተሰበሰቡበት በዚህ ወቅት፣ ድርጅቱ በታሪኩ ገጥሞት የማያውቅ ሁለንተናዊ ፈተና ውስጥ ይገኛል።

የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንደሚያስጠነቅቁት የዓለማችን ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እየከፋ የመጣው በኃያላን ሀገራት መካከል ያለው የጂኦ-ፖለቲካ ክፍፍል የጸጥታው ምክር ቤቱን ውሳኔ መስጠት እንዳይችል "ሽባ" በማድረጉ ነው።

ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደቀነው መዋቅራዊ ድክመት ከፖለቲካና ከዲፕሎማሲ አልፎ በዲጂታል ሉዓላዊነት፣ በቴክኖሎጂ እድገትና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ታዳጊ ሀገራትን የሚጎዳ ትልቅ ክፍተት ፈጥሯል።

ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የሥራ ዘመናቸው ሊጠናቀቅ በጣት በሚቆጠሩ ወራት በቀሩበት በዚህ ወቅት ድርጅቱ በአስቸኳይ መዋቅራዊ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጸጥታው ምክር ቤት አሁንም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጠናቀቀበትን የቆየ የኃይል ሚዛን የሚያንጸባርቅ እንጂ የአሁኑን የዓለም ሁኔታ አያሳይም።

ድርጅቱ ከተመሠረተ ከሰባት ዐሥርት ዓመታት በላይ ቢቆጠርም አፍሪካ በዓለም አቀፍ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የሚገባት ሚናና ተደማጭነት አሁንም ተነፍጓታል።

ይህንኑ መዋቅራዊ -ፍትሐዊነት በግንባር ቀደምትነት በመሞገት፣ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ከሁለት ያላነሱ ቋሚ ወንበሮች እና አምስት የጊዜያዊ አባልነት ወንበሮች እንዲኖሯት የአፍሪካ መሪዎች በአንድ ድምፅ እንዲጠይቁ በተደጋጋሚ ያስገነዘቡትና ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/የታሪክ ስብራትን ለማረም የዓለም አቀፍ ተቋማት ማሻሻያ የግድ እንደሆነ አስምረውበታል።

ከዚህ በተጨማሪም አፍሪካ የራሷን እውነት ለዓለም በራሷ አንደበት ማሰማት አለባት ሲሉ የሐሳብ የበላይነትን ለማረጋገጥ የአፍሪካ ህብረት አህጉራዊ የሚዲያ ተቋም (AU Continental Media House) እንዲቋቋም ጥሪ አቅርበዋል።

ኃያላን ሀገራት በራሳቸው ዓለም አቀፍ ሕጎችን እየጣሱ በጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ መሸሸጋቸው፣ መካከለኛ ኃይላት ያለ ምንም ተጠያቂነት የፈለጉትን እንዲፈጽሙ አጋጣሚ ፈጥሯል።

በመካከለኛው ምስራቅ እንዲሁም በአሜሪካ እስራኤል እና በኢራን መካከል ያለው ውጥረት፣ በሆርሙዝ ሰርጥ፣ በባቢል መንደብ እና በቀይ ባሕር አቅራቢያ የሚገኙ የባህር ላይ ንግድ መስመሮች መታወክ የነዳጅ እና የምግብ እቃዎች ዋጋ እንዲጨምር በማድረግ ታዳጊ ሀገራትን ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ውድቀት ዳርጓቸዋል።

በዩክሬን በኩል የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት መራዘም የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚን ያደቀቀ ሲሆን፣ እንደ ህንድ ያሉ መካከለኛ ኃይላት በሁለቱም ወገኖች መካከል የዲፕሎማሲ ድልድይ ለመሆን እየሞከሩ ይገኛሉ።

በተባበሩት መንግሥታት ደረጃ ከቁጥጥር ውጪ የሚወጡ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂዎችና በራሳቸው ውሳኔ ሰዎችን የሚገድሉ አውቶማቲክ መሳሪያዎች ስጋት መሆናቸው ቢነገርም፣ አሜሪካና ቻይና በጋራ ቁጥጥር ላይ ለመስማማት ፈቃደኛ አልሆኑም።

ቴክኖሎጂው በኃያላን ሀገራት እጅ ብቻ በመያዙ ምክንያት ታዳጊ ሀገራት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንጂ ፈጣሪ እንዳይሆኑ ስጋት ደቅኗል።

ይህንኑ ስጋት በመቀየር ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በብሪክስ መሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር አፍሪካ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን ንቁ ፈጣሪና አበርካች መሆን እንዳለባት አስምረውበታል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ «መደመር የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ» መመስረቷን፣ ዲጂታል መታወቂያ፣ የኤሌክትሮኒክ ክፍያና የመረጃ ጥበቃ ሥርዓቶችን መዘርጋቷን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቀጣዩ ትውልድ ኤአይ የተለያዩ ሀገር በቀል ቋንቋዎችንና እውቀቶችን ማካተት እንዳለበትም ገልጸዋል።

በአውሮፓ፣ እስያ እና አሜሪካ የታዩት የሙቀት ማዕበሎች እና ድንገተኛ የጎርፍ አደጋዎች አጣዳፊነታቸውን በመግለጽ ተመድ ልዩ የአየር ንብረት ስብሰባ ጠርቶ ይመክራል። ሆኖም በኃያላን ሀገራት የፖለቲካ ፍላጎት ማነስ ምክንያት ሁለንተናዊ ውሳኔዎችን ማሳለፍ ፈታኝ ሆኖ ቀጥሏል።

በዚህ ዓለም አቀፍ ውይይት መሃል ኢትዮጵያ በተግባር የተደገፈ ተጨባጭ መፍትሔ ይዛ በመቅረብ፣ የማድረግ አቅሟ በእጅጉ ማደጉንና በዓለም አቀፍ መድረክ ተፈላጊነቷ ከፍ ማለቱን በማስመስከር ላይ ትገኛለች።

ሀገራችን ታዳሽ ኃይልንና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት በማስተዋወቅ ወደ አረንጓዴ ቴክኖሎጂ ሽግግር እያደረገች ሲሆን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የቢሊዮን ችግኞች ተከላ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ምድርን ለማንሰራራት ፍቱን መፍትሔ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተግባር አሳይታለች።

የተባበሩት መንግሥታት ለአዲሱ ዘመን ፈተናዎች ምላሽ ለመስጠት አፋጣኝ ተቋማዊ ማሻሻያ ካላደረገ፣ የጸጥታው ምክር ቤት አወቃቀር አፍሪካን ባካተተ መልኩ ካልተቀየረ እና በቴክኖሎጂውና በአየር ንብረት ዘርፍ ፍትሐዊ ተሳትፎ ካልተረጋገጠ የዓለምን ሰላምና እድገት ማስጠበቅ ይበልጥ አዳጋች ይሆናል።

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው በቴክኖሎጂውና በአረንጓዴ ልማት ምህዳር በተግባር ያሳየችው አቋም አፍሪካ ፍትሐዊ የዓለም አቀፍ ስርዓት ለመገንባት ብቁና ዝግጁ መሆኗን ያረጋግጣል።

የተባበሩት መንግሥታት እና የዓለም አቀፍ ተቋማት የኃያላን ሀገራትን ፍላጎት ተሻግረው የኢትዮጵያንና የታዳጊ ሀገራትን እውነተኛ የፖለቲካ፣ የቴክኖሎጂ እና የአየር ንብረት ፍትሕ ድምፅ በማንጸባረቅ ተጨባጭ መፍትሔ ሊያመጡ የሚችሉት የኢትዮጵያን ዓይነት በተግባር የተረጋገጠ የማድረግ አቅም ሲከተሉ ብቻ ነው።

 

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: