Search

ቀይ ባሕር ኢትዮጵያን ለምን ይፈልጋል?

ማክሰኞ መስከረም 12, 2019 33

የኢትዮጵያ የባሕር በር መዳረሻ ጥያቄ በተደጋጋሚ የሚነሳው ከአንድ ሀገር የኢኮኖሚና የንግድ ፍላጎት አንጻር ብቻ ነው። ሆኖም ጉዳዩን በጥልቀት ለሚመረምር አካል፣ የኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ላይ መገኘት ለአንድ ወገን ብቻ የሚጠቅም ሳይሆን ለአጠቃላይ የቀይ ባሕር ቀጣና እና ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ ቀይ ባሕርን ለምን ትፈልጋለች?” ከሚለው የተለመደ ጥያቄ ባሻገርቀይ ባሕር ኢትዮጵያን ለምን ይፈልጋል?” የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ማንሳት የቀጣናውን መፃኢ እድል በአዲስ መነፅር ለመመልከት ያስችላል።

ቀይ ባሕር በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያንቀሳቅስ ወሳኝ የባሕር መስመር ቢሆንም፣ የባሕሩ አቅም ሙሉ በሙሉ ሊወጣ የሚችለው ከኋላው ባለው ሰፊ የመሬትና በግዙፍ የሕዝብ አቅም ሲደገፍ ብቻ ነው።

130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የኢኮኖሚና የሕዝብ ቁጥር ባለቤት ናት። ይህ ሰፊ ገበያ እና እያደገ የመጣው የኢንዱስትሪ ምርት ለቀይ ባሕር ወደቦች ዋና የንግድ ፍሰት ምንጭ ነው።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ቀጥተኛ መዳረሻ ሲኖራት የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ወጪ ይቀንሳል። ይህም የቀጣናውን የንግድ እንቅስቃሴ በማቀላጠፍ ለቀይ ባሕር አዋሳኝ ሀገራት የተሻለ የንግድ ፍሰትና የኢኮኖሚ ውህደት ይፈጥራል።

የቀይ ባሕር ቀጣና ዘላቂ ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው ሀገራት በጋራ ጥቅምና በሎጂስቲክስ ትስስር ሲጣመሩ ነው።

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የታዳሽ ኃይል በመጠቀም ለቀጣናው ሀገራት አረንጓዴ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።

የባሕር በር መዳረሻ ማግኘቷ እንደ የመንገድ፣ የባቡርና የኃይል መስመሮች ያሉ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን በማጠናከር የቀይ ባሕር ሀገራትን በኢኮኖሚ ያስተሳስራል።

የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግና የግብርና ምርቶች በወደቦች በኩል በቀላሉ ለዓለም ገበያ መቅረባቸው የቀይ ባሕር ቀጣናን ንቁ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ያደርገዋል።

ቀይ ባሕር በአሁኑ ወቅት የባሕር ላይ ውንብድና፣ የሕገ-ወጥ ዕቃዎችና የሰዎች ዝውውር፣ እንዲሁም የጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች ስጋት ያለበት ቀጣና ሆኗል። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አስተማማኝ ኃይል አላት።

በታሪክና በተግባር የተረጋገጠው የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር አቅምና የሰራዊቷ ጥንካሬ በቀይ ባሕር አካባቢ ለሚፈጠሩ የደኅንነት ስጋቶች አስተማማኝ ከለላ ለመስጠት ያግዛል።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ደኅንነት መዋቅር ውስጥ ተሳታፊ መሆኗ የዓለም አቀፍ የንግድ መርከቦችን ነፃና ደኅንነቱ የተጠበቀ ዝውውር ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

ቀይ ባሕር ሙሉ አቅሙን ለመጠቀም፣ የቀጣናውን ደኅንነት ለማስጠበቅና የንግድ ፍሰቱን ለማሳደግ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ አቅም ይፈልጋል። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የቀጣናውን ዘላቂ ሰላም፣ ደኅንነትና የጋራ የኢኮኖሚ ብልጽግና የሚያረጋግጥ ስልታዊ ጉዳይም ነው።

በመሆኑም የኢትዮጵያ በባሕሩ ላይ መገኘት ለቀይ ባሕር አካባቢ ሀገራትና ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተጨማሪ አቅምና የጋራ እድገት ዋስትና ነው።

 

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: