Search

"የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የልማትና የትራንስፖርት ትስስር የሕዝቦችን ሕይወት የመቀየር አቅሙ ከፍተኛ ነው"፦ የተባበሩት መንግሥታት

ማክሰኞ መስከረም 12, 2019 51

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዚዳንት  ኻሊሉር ረህማን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሀብት ድልድሉንና አጠቃቀሙን በአግባቡ ማስተካከል እንዳለበት ጥሪ አቀረቡ።

ፕሬዚዳንቱ እንዳመለከቱት ልማትን ለማፋጠንና ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት የልማት እርዳታዎችን ማሳደግ፣ የዕዳ ጫናዎችን ማቃለል እንዲሁም የዓለም አቀፉን የፋይናንስ መዋቅር ማሻሻል ወሳኝና አስቸኳይ ጉዳይ ነው።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ወቅት በተለይም የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት ቃልኪዳኖችን ማክበር እንደሚገባና ዝቅተኛ የልማት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሀገራት፣ የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት እና የደሴት ሀገራት የተነደፉ የድርጊት መርሃ ግብሮችን በትክክል መተግበር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ግቦችን ለማሳካት የተቀናጀ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የባህር በር የሌላቸው ሀገራትን ጨምሮ ለታዳጊ ሀገራት የሚደረጉ ልዩ ልዩ የልማትና የትራንስፖርት ትስስር ድጋፎች የሕዝቦችን ሕይወት የመቀየር አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑን ያመላከቱት ፕሬዚዳንቱ፣ ትኩረት በተሰጠባቸው ዘርፎች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ብቻ ወደ 1 ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ንጹህና ደህንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውሃ ማግኘት መቻላቸውን፣ የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚነት 92 በመቶ በመድረስ ሙሉ በሙሉ ተዳራሽ ለመሆን መቃረቡን እንዲሁም የኢንተርኔት ተደራሽነት 40 በመቶ ወደ 74 በመቶ ማደጉን አብራርተዋል።

 

ይህ አዎንታዊ አቅጣጫ የሚያሳየው ዓለም አቀፍ ትብብርና የፋይናንስ ስርዓት ማሻሻያ በትክክል ከተተገበረ የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራትን ጨምሮ የበርካታ ሀገራትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት በላቀ ደረጃ ማፋጠን እንደሚቻል ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: