Search

ኢትዮጵያ በተግባር፡ ከታሪክ ባለጸጋነት እስከ ዘመናዊ የቱሪዝም ማዕከልነት

ረቡዕ መስከረም 13, 2019 173

ኢትዮጵያ ከቀደምት የታሪክ እና የቅርስ ባለቤትነቷ ባሻገር፣ የቱሪዝም መዳረሻዎቿን በዘመናዊ መልክ በማልማት ትልቅ የመፈጸም ዐቅሟን ለዓለም እያስመሰከረች ነው።

ዓለም ኢትዮጵያን ያውቅበት ከነበረው ጠባብ ትርክት በመውጣት፤ ዛሬ ላይ በልማት፣ በውበት እና በእንግዳ ተቀባይነት እጅግ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ በተግባር እያሳየች ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "እንግዳ ሲመጣ የት እወስደዋለሁ ብዬ አልጨነቅም" ሲሉ የገለጹት ሐሳብ፣ በአጭር ጊዜ የተለወጡ መዳረሻዎችን፣ ውብ የኮሪደር ልማቶችን እና የተጨበጡ የገጽታ ለውጦችን በሚገባ የሚወክል እውነታ ነው።

በከፍተኛ የተቋም ብቃት እና በሀገር ፍቅር ስሜት የተከናወኑት የ"ገበታ መርሐ ግብሮች ይህንን ዐቅም በተግባር አረጋግጠዋል።

በ"ገበታ ለሸገር" የተከናወኑት የከተማ ወንዞች ልማት፣ መናፈሻዎች እንዲሁም እንደ አድዋ ድል መታሰቢያ ያሉ ግዙፍ ማዕከላት አዲስ አበባን ይበልጥ አስውበዋታል።

በ"ገበታ ለሀገር" እና "ገበታ ለትውልድ" ደግሞ እንደ ወንጪ፣ ጎርጎራ፣ ኮይሻ እና ሀላላ ኬላ ያሉ እጅግ ማራኪ የተፈጥሮ ቱሪዝም መዳረሻዎች ተገንብተው እንግዶችን በአዲስ ድምቀት መቀበል ጀምረዋል።

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የተከናወኑት እነዚህ ታላላቅ ፕሮጀክቶች፣ ኢትዮጵያ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ያለምንም እንከን በማስተናገድ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ ማዕከል እንድትሆን አድርገዋታል።

ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰፊ የበረራ ትስስር እና የተስፋፉ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች ሲደመሩበት፤ ዓለም አቀፍ እንግዶች እና ባለሙያዎች ከስብሰባ ጎን ለጎን የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል።

በዘርፉ የታየው ይህ የላቀ አፈጻጸም፣ ቱሪዝም ከባህል እና ታሪክ እሴትነቱ አልፎ ዋነኛ የኢኮኖሚ ሞተር እንዲሆን አስችሎታል።

የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ፣ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉን ገቢ በማስፋት የኢኮኖሚ ዕድገትን እያረጋገጠ ይገኛል።

የትናንትናው ታሪካዊ ቅርስ ባለቤትነታችን ከዛሬው ዘመናዊ የልማት አፈጻጸም ጋር ተጣምሮ፤ ኢትዮጵያን በዓለም ደረጃ ተመራጭ የቱሪዝም፣ የኮንፈረንስ እና የኢንቨስትመንት ማዕከል እያደረጋት ነው።

በሔዋን ጌታቸው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: