Search

ጽኑ የሰማይ ላይ ዋስትና፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የዘጠኝ አስርት ዓመታት የከፍታ ጉዞ

ረቡዕ መስከረም 13, 2019 147

የአንድ ሉዓላዊ ግዛት የጽናት ማዕዘን የሚለካው ወሰኑን እና አየር ክልሉን በሚጠብቅበት አስተማማኝ አቅም ነው።

ላለፉት ዘጠኝ አስርት ዓመታት የሀገራችንን አየር ክልል በንቃት የጠበቀው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፤ ዛሬ ላይ ታሪካዊ ጀግንነቱን ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር አስተሳስሮ ወደ ላቀ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

ተቋሙ ሰማይን ከመጠበቅ ባሻገር ኢትዮጵያ በኤሮስፔስ እና በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ያላትን ሰፊ አቅም ለዓለም እያስመሰከረ ይገኛል።

በአፍሪካ አህጉር በግንባር ቀደምትነት ከተቋቋሙት ዘመናዊ የአቪዬሽን ተቋማት አንዱ የሆነው አየር ኃይላችን ባለፈባቸው የፈተና እና የድል መንገዶች ሁሉ የኢትዮጵያን ጽናት በደማቁ አንጸባርቋል።

በተለይም መከላከያ ሠራዊቱ ስትራቴጂያዊ ኢንቨስትመንቱን አቅጣጫ በማሻሻል ተቋሙን በዘመናዊ አቪዬሽን ቴክኖሎጂዎች እና በትጥቅ የማደራጀት ሰፊ ሥራ ሰርቷል።

የቅርብ ጊዜዎቹን ባለብዙ ተልዕኮ ተዋጊ ጀቶች እና አዳዲስ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጨምሮ ዘመናዊ ሄሊኮፕተሮችን በመታጠቅ የውጊያ፣ የስለላ እና የመከላከል አቅሙን አጠናክሯል።

አየር ኃይሉ የአፍሪካ ቀንድን ሰላም በማስጠበቅ እና የሽብርተኝነት ስጋቶችን በመቀልበስ ረገድ የማይተካ ቀጣናዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

የቴክኖሎጂ ጥገኝነትን ለመቀነስ በወሰደው ርምጃ፤ በወጣት ኢትዮጵያውያን መሃንዲሶች እና ቴክኒሻኖች አማካኝነት ተዋጊ ጀቶችን፣ የትራንስፖርት እና የውጊያ ሄሊኮፕተሮችን በራስ አቅም የማደስ፣ የመጠገን እና የማዘመን ሥራዎችን በስፋት እያከናወነ ነው።

በዘመናዊው የአቪዬሽን ሳይንስ ውስጥ የሚታየው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አጠቃቀምም ተቋሙ ከዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ፍጥነት ጋር እኩል እየተራመደ መሆኑን ያረጋገጠ ነው።

የአየር ኃይሉ የአቪዬሽን ትምህርት ቤቶች እና የምርምር ማዕከላት በኤሮስፔስ፣ በኮዲንግ እና በራዳር ቴክኖሎጂዎች የሠለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ለኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ እመርታ ጠንካራ መሰረት ጥለዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያለፉትን 90 ዓመታት ታሪካዊ ታማኝነቱን ሳያጎድል ዛሬ ላይ በራስ አቅም በሚያዘምናቸው ሄሊኮፕተሮች፣ በዘመናዊ ተዋጊ ጀቶቹ እና በቴክኖሎጂ ምጥቀቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ክብር ከፍ ያደረገ ኩራት ነው።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: