Search

የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ፡ ከዕውቀት ወደ ተጨባጭ ፈጠራ

ረቡዕ መስከረም 13, 2019 128

የቴክኖሎጂ ለውጥ የዘመናዊ ዓለምን አቅጣጫ ከመቀየር ባለፈ የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ የሥራ ፈጠራን እና የመንግሥት አገልግሎትን የሚወስን ዋነኛ ኃይል ሆኗል።

ኢትዮጵያም ይህን የዓለም አቀፍ መነቃቃት ቀድማ በመረዳት ቴክኖሎጂን ከልማት ጋር በማስተሳሰር የዲጂታል ሽግግሯን ለማፋጠን ሰፊ የለውጥ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች።

በስኬት የተጠናቀቀው "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ስትራቴጂ ለዚህ ዲጂታል ጉዞ ጠንካራ መሠረት ጥሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ይህንን ስኬት አጠናክሮ ኢትዮጵያን ወደ ዕውቀት መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያስችለው "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂ ወደ ትግበራ ገብቷል።

ይህ አዲሱ ራዕይ በተለይም በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) በዳታ ሳይንስ እና በዲጂታል ክህሎት ግንባታ ላይ ልዩ ትኩረት የሰጠ ነው።

የነገው ኢኮኖሚ በተፈጥሮ ሀብት ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ አቅም ጭምር የሚወሰን በመሆኑ ይህን የሚመጥን ትውልድ ማነጽ የረጅም ጊዜ የልማት ግብ አካል ሆኗል።

የቴክኖሎጂ ሽግግሩ በአየር ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን በተጨባጭ ሕይወት ውስጥ የሚታይ ነው።

ዛሬ ላይ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች እንደ 'ቴሌብር' በመሳሰሉ የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎች የዜጎችን የዕለት ተዕለት ግብይት አቅልለዋል።

የብሮድባንድ ኢንተርኔት እና '5G' ቴሌኮም አገልግሎት መስፋፋት፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ስታርታፖች መበራከት ለወጣቱ አዳዲስ የሥራ እድሎችን የሚፈጥር ጠንካራ መደላድል ዘርግተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በተለያዩ መድረኮች አጽንኦት እንደሚሰጡት ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን የዕውቀት እና የፈጠራ ባለቤት መሆን አለባት።

ይህንንም በተግባር ለማሳየት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በመሳሰሉ ተቋማት በኩል ሀገራችን በምርምር፣ በቴክኒክ ክህሎት እና በመፍትሔ አመንጪነት በአፍሪካ አህጉር የራሷን አሻራ እያሳረፈች ነው።

ቴክኖሎጂን ማስፋፋት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ፣ ከዲጂታል ሽግግሩ ጋር አብሮ የመጣውን የሳይበር ደኅንነት መጠበቅ የብሔራዊ ደኅንነት ዋነኛ አካል ሆኗል።

የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን እና የዜጎችን መረጃ ከሳይበር ስጋቶች መከላከል ወሳኝ ተግባር ነው።

ከዚህም ባሻገር የዲጂታል አጠቃቀማችንን ከኢትዮጵያዊ ባህል፣ እሴት እና ሉዓላዊነት ጋር በተናበበ መልኩ ማስተካከል ልዩ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው። ይህም የዲጂታል ልማት ከማኅበረሰብ ሥነ-ልቦና ጋር ተዋሕዶ እንዲጓዝ አስችሏል፡፡

ይህ ዘርፈ ብዙ ሽግግር በትምህርት ሥርዓቱም ላይ አዲስ በር ከፍቷል። የትምህርት ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ የመማር ማስተማር ሂደትን በማስፋፋት፣ ጥራት ያለውን ዕውቀት በቦታ ሳይገደቡ በተለያዩ ቋንቋዎች ለተማሪዎች በማድረስ ላይ ይገኛሉ።

ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል የፈጠራ እና የዘመናዊነት ማሳያ እየሆነ መምጣቱን በቅርቡ ካየነው ክስተት መረዳት ይቻላል።

2019 . አዲስ ዓመትን ስንቀበል 3 ሺህ በላይ ድሮኖች በሰማይ ላይ የሳሉት ደማቅ የብርሃን ትዕይንት፣ የመዝናኛ ትርዒት ብቻ ሳይሆን የሀገራችንን አዲስ የቴክኖሎጂ አስተሳሰብ እና ከፍታ ያሳየ ድንቅ ምሳሌ ነበር።

የወደፊቷ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዕውቀት የታነጸች፣ በፈጠራ የምትመራ እና የራሷን የቴክኖሎጂ መፍትሔዎች የምታመነጭ እንድትሆን የተያዘው ራዕይ ዕውን እየሆነ ነው።

ይህን ጉዞ ይበልጥ ለማፋጠን ደግሞ የመንግሥት፣ የግል ዘርፉ፣ የትምህርት እና ምርምር ተቋማት እንዲሁም የፈጣሪው ወጣት የጋራ ርብርብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ወሳኝ ነው።

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: