ለቀጣዩ ትውልድ አርአያ የሚሆኑ ጀግኖችን ታሪክ መጻፍ እና ማሻገር ለሀገር ግንባታ ወሳኝ መሆኑን የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናግረዋል።
ኢታማዦር ሹሙ ይህንን የተናገሩት የሕይወት እና የውትድርና ጉዟቸውን የሚያስቃኘው “ድል ቁርሱ” የተሰኘ መጽሐፍ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው።
ፊልድ ማርሻሉ እንዳሉት፣ እንደ በላይ ዘለቀ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ እና አብዲሳ አጋ ያሉ አኩሪ ጀግኖችን ታሪክ ከሞት በኋላ ማስታወስ መልካም ቢሆንም፣ አሁን በሕይወት ያሉ ሀገር ያቆሙ እና ለሉዓላዊነት ዋጋ የከፈሉ የመከላከያ መሪዎችን ታሪክ በጽሑፍ አስፍሮ ማቆየት ለነገው ተተኪ ትውልድ ጠንካራ የሀገር ወዳድነት መሠረት ይጥላል።
በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የነበሩ እና አሁንም ያሉ ከፍተኛ የጦር መሪዎች ታሪካቸውን በጽሑፍ የማስቀመጥ ክፍተት እንዳለ የጠቆሙት ጠቁመዋል፡፡
ለአብነትም እንደ ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ ያሉ የጦር መሪዎች የነበራቸውን የውጊያ ልምድ፣ የዲፕሎማሲ ተሳትፎ እና የሕይወት ገጠመኝ በምርምር እና በታሪክ ሰነድነት ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በተመሳሳይ ሌሎች ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎች እና መኮንኖችም ታሪካቸውን በጽሑፍ በማስፈር ተመሳሳይ ተግባር እንዲፈጽሙ ጥሪ አቅርበዋል።
የታሪክ እና የትምህርት መጻሕፍት ሲዘጋጁ ዋና ትኩረታቸው ሀገር ወዳድ ዜጋን መቅረጽ መሆን እንዳለበት የጠቀሱት ኢታማዦር ሹሙ፣ ከመጻሕፍት ሽያጭ የሚገኝ ገቢም ለንግድ ወይም ለግል ጥቅም ከመዋል ይልቅ የተቸገሩ ወገኖችን ለመደገፍ እና ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት መዋል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: