Search

የኢትዮጵያ የልማት እና የመፈጸም አቅም ከተግባራዊ ስኬት እስከ ሉዓላዊ ከፍታ

ረቡዕ መስከረም 13, 2019 132

ታሪክ እንደሚነግረን ሀገራት ከተጋረጡባቸው ውስብስብ ፈተናዎች ተላቅቀው ወደ ዘላቂ ብልጽግና ለመሸጋገር የሚያደርጉት ጥረት የሚመዘነው በወረቀት ላይ ባሰፈሯቸው ዕቅዶች ብቻ አይደለም።

ይልቁንስ ዕቅዶቻቸውን በመሬት ላይ ለመተግበር በሚያስላቸው ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (/) በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደሚናገሩት ሀገር የምትቀየረው በሰነዶችና በፖሊሲዎች ብዛት ሳይሆን መሬት የወረዱ እና በተግባር የተተገበሩ ተጨባጭ ፕሮጀክቶች ሲኖሩ ነው።

በዚህ ዕሳቤ መሠረት ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በልማት፣ በተቋማት ግንባታ እና ራስን ከተረጂነት በማውጣት ረገድ የከፈተችው አዲስ ምዕራፍ ይህንኑ የማድረግ አቅም በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ በምግብ እርዳታ ጠያቂነት እና በተረጂነት ትታወቅ የነበረችበትን የቆየ ታሪክ ለመቀየር ስር ነቀል ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።

የግብርናው ዘርፍ ስኬቶች ደግሞ የዚሁ አቅጣጫ ዋና ማሳያ ናቸው። ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት አላቅቆ በበጋ እና ክረምት የመስኖ ስንዴ ልማት እንዲሁም በኩታ ገጠም እርሻ ማገዝ በመቻሉ፣ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራስን ከመቻል አልፋ ወደ ውጭ ኤክስፖርት ማድረግ የምትችልበት ደረጃ ላይ ደርሳለች።

በሰብል፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተከናወኑት ተግባራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ጥለዋል።

እነዚህ ውጤታማ እርምጃዎች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የኖረውን የቀደመ የተረጂነት ምስል እንድትቀይር መንገድ ከፍተውላታል።

ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ አስተማማኝ እና ጠንካራ ተቋማት መኖራቸው የግድ በመሆኑ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድም ሰፊ እና መዋቅራዊ ሥራዎችን አከናውናለች።

በተለይም በጸጥታ እና ደኅንነት ዘርፍ የተከናወኑት የተቋም ግንባታ ሥራዎች ሀገራችን የውስጥ ሰላሟን ለመጠበቅ እና ቀጠናዊ ድርሻዋን ለመወጣት ያላትን አቅም አሳይተዋል።

የመከላከያ ሠራዊትና የደኅንነት ተቋማትን በሰው ሀብት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በትምህርት በማደራጀት ኢትዮጵያ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የባሕር ኃይልን ጨምሮ የቀጣናውን ዘላቂ ሰላም ለመጠበቅ የሚያስችል ጽኑ መሠረት መጣሏን አረጋግጣለች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የከተሞች የኮሪደር ልማት እና የዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም መዳረሻዎች ግንባታ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በራስ አቅም መከናወናቸው በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ የኢትዮጵያን ተሰሚነት አሳድገውታል።

ባለፉት ዓመታት የታየው ይህ የልማት፣ የመሠረተ ልማት እና የተቋማት ግንባታ ጉዞ የኢትዮጵያን የማድረግ አቅም በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት እና ፕሮጀክቶችን የመፈጸም ብቃት ከተገነባ ከተረጂነት መውጣት እንደሚቻል ያሳየው ይህ አዲስ ምዕራፍ፣ የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያ መልክ ቀድሞ ያሳየ ብሩህ መንገድ ነው።

በዓይናለም ሀድራ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: