የታሪክ፣ የባህል እና የአካባቢው መለያ ስያሜ መገኛ የሆነው የዳሞታ ተራራ የመጀመሪያ ምዕራፍ የኢኮ-ቱሪዝም ልማት ፕሮጀክት ተጠናቅቆ ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል።
የዳሞታ ተራራ በርካታ ብዝኃ ሕይወትን፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን ብርቅዬ መስህቦች አቅፎ የያዘ ተፈጥሮአዊ ጸጋ ነው።
ተራራው ለዘመናት የልማት እይታ አጥቶ በመቆየቱ ምክንያት በእቅፉ የያዛቸውን እምቅ ሀብቶች በአግባቡ ማወቅና መጎብኘት ሳይቻል ቆይቷል።
ሆኖም ለቱሪዝም ዘርፉ በተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እና በ"መደመር" የልማት ኢኒሼቲቭ አማካኝነት፣ የተራራውን የተሸሸጉ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ጸጋዎች በመለየት ማልማት ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት የስፍራውን ሳቢነት እና ማራኪነት ይበልጥ ለማጎልበት የሕዝብ እና የግል ባለሀብት ቅንጅት በተግባር እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን፣ የወላይታን ጥንታዊ ባህልና ታሪክ በሚያንጸባርቅ መልኩ የተገነባው "ካዎ ሎጅ" አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የከተማዋ "ባለ ሰባት በር" የንግድ እና ኢንቨስትመንት ስያሜም ከፕሮጀክቱ ጋር ተሰናስሎ ለስፍራው ተጨማሪ ድምቀት ሆኗል።
በተጨማሪም ጎብኚዎች እና የስፖርት አፍቃሪያን በቀላሉ ወደ ተራራው አናት መውጣት እንዲችሉ ታስቦ እስከ ተራራው ጫፍ የሚደርሱ 7 ሺህ 187 መወጣጫ ደረጃዎች ግንባታ ተካሂዷል።
የዚህ ታላቅ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ በስኬት መጠናቀቁን ተከተሎ ስፍራው ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች ክፍት ሆኗል።
የዳሞታ ተራራ 12 ሺህ 500 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን፣ ከባሕር ጠለል በላይ 2 ሺህ 750 ሜትር ከፍታ እና ከ68 ኪሎ ሜትር በላይ የዙሪያ ርቀት ያለው ታላቅ ተፈጥሮአዊ ሀብት ነው።
ለረጅም ጊዜ ሲያቀርቡት የነበረው የማልማት ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱና ቀደም ሲል ተሸፍነው የቆዩ የመዳረሻ ስፍራዎች በመልማታቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ታላቅ ደስታቸውን ገልጸዋል።
የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማልማት እና የማሳደግ ጥረት በአካባቢው በቅንጅት እየተገበሩ ከሚገኙ ሌሎች የልማት መስኮች ጋር ተጣጥሞ የወለይታ ዞን የኢኮኖሚ እና የቱሪዝም እንቅስቃሴ እያሳደገው ይገኛል።
በትዕግስቱ ቡቼ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: