Search

የኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ምርት የታገዘ የኢኮኖሚ እና ብሔራዊ ሉዓላዊነት ጉዞዋ

ሓሙስ መስከረም 14, 2019 169
በዘመናዊው ዓለም የአንድ ሀገር እውነተኛ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር የሚለካው በፖለቲካዊ ውሳኔዎቿ ነፃነት ብቻ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚዋ ጥንካሬና ራሷን የመቻል አቅሟ ጭምር መሆኑ እየጎላ መጥቷል።
በዓለም አቀፍ የጂኦፖለቲካዊ ውጥረት፣ የንግድ ሽኩቻና ያልተጠበቁ ቀውሶች በበዙበት በዚህ ዘመን፣ የውጭ ሸቀጦችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት (Import Substitution) የሕልውና ጉዳይ ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ እንዳመላከቱት፣ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከውጭ ጥገኝነት በመላቀቅ የሀገር ውስጥ አቅምን ወደ መገንባት በተኪ ምርት የተሳካ ሽግግር እያደረገ ይገኛል።
በዚህም የመደመር መንግሥት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት አሁን ላይ አጠቃላይ የማኑፋክቸሪንግ የማምረት አቅም በኢትዮጵያ ታምርት ብሔራዊ ንቅናቄ በመመራት፣ የፋብሪካዎች የማምረት አቅም ወደ 67 በመቶ ማሳደግ ተችሏል።
የውጭ ምርት ጥገኝነትን መቀነስ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ ብቻ ሳይሆን፣ በማንኛውም ዓለም አቀፍ ጫና ውስጥ የማትንበረከክ፣ የጸናችና የተከበረች ሀገር ለመገንባት መሠረታዊ ዋስትና ነው።
የውጭ ሸቀጦችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የሀገር ውስጥ አምራቾችንና ኢንዱስትሪዎችን አቅም በማጎልበት ይጀምራል።
አበይት የፍጆታና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ሲጀመር የአምራች ኢንዱስትሪዎች፣ የአግሮ-ፕሮሰሲንግና የቴክኖሎጂ ተቋማት መስፋፋት ለሚሊዮኖች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
በተጨማሪም ለውጭ ምርቶች ይወጣ የነበረው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በሀገር ውስጥ በመቅረቱ ለሌሎች ስትራቴጂካዊ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲያውል ያስችላል።
የሀገር ውስጥ ምርት ጥራትና ብዛት ሲጨመር የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ክህሎትና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አቅም አብሮ ያድጋል። በምግብ፣ በመድኃኒትና በመሠረታዊ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች በሌሎች ሀገራት ላይ ጥገኞች መሆን ሀገራዊ ደኅንነትን ለደጋፊዎች ወይም ለላኪዎች ፈቃድ አሳልፎ መስጠት ነው።
የውጭ ሀገራት ወይም ዓለም አቀፍ ተቋማት የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ጫና ለማሳደር ከሚጠቀሙባቸው ዋነኛ መሳሪያዎች አንዱ የንግድ ማዕቀብና የምርት እገዳ ነው። ሀገር በቀል የምርት አቅምን ማሳደግ ግን ይህንን ተጋላጭነት በዘላቂነት ያስወግዳል።
አንድ ሀገር መሠረታዊ ፍላጎቶቷን በራሷ አቅም ማሟላት ስትችል ከማንኛውም አካል የሚመጣን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫና ሳትሰጋ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብሩ ውሳኔዎችን በነፃነት መወሰን ትችላለች።
እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የገበያ መዛባቶች፣ የጦርነትና የበሽታ ቀውሶች በሀገራችን የዕለት ተዕለት ህይወት ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ አነስተኛ ይሆናል።
የውጭ ሸቀጦችን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ራዕይ እንዲሳካ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል። መንግሥት ለአምራች ዘርፉ የመሠረተ ልማት፣ የፋይናንስና የፖሊሲ ድጋፎችን በማመቻቸት፣ አምራቾች ደግሞ የምርቶቻቸውን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የሕዝቡ የፍጆታ ባህል ተለውጦ "የሀገሬን ምርት እጠቀማለሁ" የሚል ሀገራዊ ፍቅርና ኩራት ማደግ አለበት።
የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ውድድርን የመሸሽ ጉዳይ ሳይሆን፣ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥና የሀገርን ሕልውና የማጽናት ጉዳይ ነው።
የራሷን ምግብ የምታመርት፣ የመሠረታዊ ሸቀጦቿን ፍላጎት በራሷ የምታሟላና የኢንዱስትሪ አቅሟን ያሳደገች ሀገር በማንኛውም ዓለም አቀፍ ማዕበልና ጫና ውስጥ የማትንበረከክ የጸናች ሀገር ትሆናለች።
ሀገራዊ ሉዓላዊነት በፖለቲካ መድረክ ብቻ ሳይሆን በፋብሪካዎች፣ በእርሻ ማሳዎችና በፈጠራ ማዕከላት ውስጥም ይገነባል።
በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: