በኒውዮርክ እየተካሄደ ከሚገኘው 81ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን፣ በኢትዮጵያ የተመዘገበው የዲጂታል ፋይናንስ አካታችነት የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማፋጠን እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ የሚያሳይ ከፍተኛ የምክክር መድረክ ተካሄደ።
በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፎ በተካሄደው በዚህ መድረክ፣ የሀገራችን የዲጂታል ሽግግር ስኬቶች እና የወደፊት አቅጣጫዎች በሰፊው ተዳስሰዋል።
በኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ መሥሪያ ቤት እና በተባበሩት መንግሥታት የካፒታል ልማት ፈንድ አዘጋጅነት በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ ሚኒስትሮች፣ የልማት አጋሮች እና የፋይናንስና የቴክኖሎጂው ዘርፍ የግል ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።
በመድረኩም በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ያለው የፈጠራ ሥነ ምህዳር፣ የ"ፋይዳ" ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ትግበራ፣ የፈጣን ዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ሽግግር እና የመንግሥት የዲጂታል ሕዝባዊ መሠረተ ልማት እንቅስቃሴዎች በዋናነት ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
በውይይቱ እነዚህ የፖሊሲ ዕርምጃዎች ለአዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎች፣ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ለኢንተርፕራይዞች እድገት እና ለዜጎች የኑሮ ደረጃ መሻሻል አዳዲስ አማራጮችን እየፈጠሩ መሆኑም ተመላክቷል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በመክፈቻ ንግግራቸው፣ ኢትዮጵያ ያከናወነችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እንዲሁም ለዲጂታል ክፍያዎች፣ ለዲጂታል መታወቂያ እና ለሕዝባዊ አገልግሎቶች መሠረታዊ ሥነ-ምህዳር በመገንባት ረገድ ያስመዘገበችውን ከፍተኛ ስኬት አብራርተዋል።
በመድረኩ የተሳተፉት የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የዲጂታል ፋይናንስ አካታችነትን እንደ ዋነኛ መሣሪያ በመጠቀም ረገድ የነደፈቻቸውን ጠንካራ የፖሊሲ ማዕቀፎችና ያስመዘገበችውን እድገት ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም ዲጂታል ፋይናንስን በቀላሉ ከምርትነት ባለፈ እንደ ሀገራዊ መሠረተ ልማት የመመልከት ሀገራዊ አቅጣጫ መያዙን ገላጸዋል፡፡ ይህም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030፣ በብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ፣ በፋይዳ መታወቂያ፣ በቅንጅታዊ የክፍያ ሥርዓቶች እና በ«BRIDGE 2030» ማዕቀፎች የተደገፈ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የዲጂታል ፋይናንስ አካታችነት ያለውን የኢኮኖሚ ፋይዳ፣ አሳታፊነትን እና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ያለውን ላቅ ያለ ሀገራዊ ፋይዳ አብራርተዋል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት የካፒታል ልማት ፈንድ ኤክስኪዩቲቭ ሴክሬተሪ ፕራዲፕ ኩሩኩላሱሪያ በታዳጊ ሀገራት ያሉ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረቶችን በመጠቆም አነስተኛና አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንዲስፋፉና የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ የካፒታል አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ የኢኮኖሚ ልማት ረዳት ዋና ጸሐፊ ናቪድ ሀኒፍ፣ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን አበረታች እድገት አድንቀው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና የፋይናንስ አካታችነት ለአጠቃላይና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ልማት ያለውን ሁለንተናዊ አስፈላጊነት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
በአጠቃላይ ይህ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የጎንዮሽ መድረክ ፣ከዲጂታል አጠቃቀም ባለፈ ወደ ምርታማ ትግበራ መሸጋገርን እንዲሁም ሀገር በቀል ስኬታማ የፈጠራ ሥራዎችን በጠንካራ ኢንቨስትመንት፣ በስልታዊ እና በቀጣናዊ ትብብሩ ውህደት አማካኝነት አቅምን ማሳደግና ማስፋፋት የሚችሉ መፍትሔዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥቷል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: