ኢትዮጵያ በታሪኳ ለነጻነቷና ለሉዓላዊነቷ የከፈለችው መስዋዕትነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ ስፍራ የሚሰጠው ነው። የዚህች ታሪካዊት ሀገር ሉዓላዊነትና ክብር ሳይደፈር እስከ ዛሬ ሊዘልቅ የቻለው ደግሞ በየዘመናቱ በደሙና በአጥንቱ ሀገርን ባቆመው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ነው።
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሕልውና መሠረት፣ የሕዝብ ደኅንነት ዋስትና እና የሀገር ፍቅር መገለጫ የሆነ ተቋም ነው።
የሠራዊቱ ታሪካዊ መሠረት ከሀገራችን የነጻነት ጉዞ ጋር በጥብቅ ተሳስሯል። ከዓድዋ የነጻነት ተጋድሎ እስከ ዘመናዊው የመከላከያ ግንባታ ድረስ፣ ሠራዊቱ የሀገርን ዳር ድንበር የማስከበር ተልዕኮውን በብቃት ሲወጣ ቆይቷል።
በታሪክ አጋጣሚዎች የውጭ ወራሪዎች የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለመድፈር ሲሞክሩ፣ ሠራዊቱ በተለያየ መልኩ ተደራጅቶና ተሰልፎ መስዋዕትነት በመክፈል ሀገርን አስከብሯል።
ይህ ታሪካዊ አደራ ዛሬም ድረስ ቀጥሎ፣ ዘመናዊ የውጊያ ታክቲክን፣ ቴክኖሎጂንና ሳይንሳዊ አሰራርን በማቀናጀት የሀገርን የሰማይና የምድር ድንበር በጥንካሬ የመጠበቅ ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል።
አንድን ሠራዊት በውጊያ ሜዳ ውጤታማ ከሚያደርጉት ዋና ዋና ነገሮች መካከል የወታደራዊ ሙያ እና የሞራል ልዕልና ግንባታ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሚያንፀባርቃቸው ቁልፍ የሞራል እሴቶች፣ ከግልና ከቡድን ጥቅም ይልቅ የሀገርን ሕልውና እና የሕዝብን ሰላም ማስቀደም፣ በከፍተኛ የሥነ-ምግባር ደንብ መመራት፣ ለህግ እና ለሰብዓዊ መብቶች ተገዢ መሆን እንዲሁም የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ውክልና ያለበትና የጋራ ዓላማን አንግቦ የሚሰለፍ ጠንካራ ወታደራዊ ቤተሰብ መሆን ተጠቃሽ ናቸው።
እነዚህና መሰል እሴቶች ሠራዊቱ የትኛውንም ዓይነት ፈተና ተቋቁሞ ለተሰጠው ግዳጅ በብቃት እንዲቆም የሚያስችሉት አዕምሯዊና መንፈሳዊ ጥንካሬዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት በታሪክ የፃፋቸው የጀግንነት ገድሎች በሀገር ውስጥ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም። በሀገር ውስጥ የሀገርን ሰላም ለማስከበርና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስጠበቅ ካደረጋቸው ተጋድሎዎች ጎን ለጎን፣ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችም የደመቀ ስም አለው።
በአሁኑ ወቅታዊ ሁኔታ፣ የሀገር ሉዓላዊነት ከድንበር ጥበቃ ባለፈ ውስብስብ ጥቃቶችን እና የውስጥ ደኅንነት ስጋቶችን የመከላከል ሥራን ይጨምራል።
በዚህም የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ሀገርን ለማፍረስና የሕዝብን ሰላም ለማደፍረስ የሚሰሩ እኩይ ኃይሎችን በመመከት የሀገርን ሕልውና ያረጋግጣል።
ሰላምና ዘላቂ መረጋጋት በሌለበት የኢኮኖሚ ልማትን ማሰብ ስለማይቻል፣ ሠራዊቱ የሚያስከብረው ሰላም ለሀገራችን እድገት መሠረት ነው።
ወቅቱን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ የስለላና የመረጃ አቅሙን በማሳደግ የማንኛውንም ስጋት ስፋትና ጥልቀት አስቀድሞ የማክሸፍ ሥራ ይሰራል።
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ፍቅርን በተግባራዊ ጀግንነትና መስዋዕትነት የጻፈ፣ የሀገር ሕልውና የማዕዘን ድንጋይ ነው።
ታሪካዊ ውርሱን ከዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስና የሞራል ልዕልና ጋር በማጣመር የሚያደርገው ጉዞ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የሕዝቦቿን ሰላም አስተማማኝ በሆነ መሠረት ላይ እንዲቆም አድርጎታል።
የሠራዊቱ ጥንካሬ የሀገር ጥንካሬ፣ የሠራዊቱ ክብር ደግሞ የሙሉ ኢትዮጵያውያን ክብር ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: