የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ ለዘመናት ሲፈተንበት የኖረው ካለፈው ስህተት ተምሮ የተሻለውን በማስቀጠል ላይ ከመመሠረት ይልቅ ሁሉንም ነገር ከዜሮ የመጀመር ባህል ነው።
ከዘውዳዊው ሥርዓት እስከ ደርግ፣ ከደርግ እስከ ኢሕአዴግ በነበሩት የሥርዓት ሽግግሮች አዲስ መንግሥት ሲመጣ የቀድሞውን ተቋማዊ ዐሻራ ማጥፋት እና ማፍረስ እንደ ልማድ ሲቆጠር ቆይቷል።
በጠብመንጃ አፈሙዝ ላይ የተመሠረተው ይህ የፖለቲካ ልምምድ፣ ሀገራችንን ማለቂያ ለሌለው ውዝፍ ዕዳ ዳርጓታል። የጸጥታ እና ደኅንነት ተቋማትን ጨምሮ ጠንካራ ተቋማት በየጊዜው ሲፈርሱ እና እንደ አዲስ ሲዋቀሩ፣ የተማረ እና የዳበረ አቅም እየባከነ ሀገረ መንግሥቱ በተረጋጋ መሠረት ላይ እንዳይቆም ዋጋ አስከፍሏል።
ይሁንና የመደመር መንግሥት ይህንን አፍራሽ ትርክት በመቀየር አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። የተበላሹ አሠራሮችን በማረም ያሉትን አቅሞች በማጎልበት እና ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ላይ ያተኮረው ይህ ዕሳቤ የጸና ሀገረ መንግሥት መገንባት የሚቻለው በግለሰቦች ጠንካራነት ወይም በጊዜያዊ ፖለቲካዊ ሁነቶች ላይ ሳይሆን ራሳቸውን በቻሉ እና በማይናወጡ ተቋማት ላይ መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል።
ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ የሆኑ የፍትሕ፣ የደኅንነት እና የዴሞክራሲ ተቋማት የቡድን ፍላጎት ከማስፈጸም ወጥተው የሀገር ሉዓላዊነትን እና የሕዝብን ደኅንነት ለማስጠበቅ የጀርባ አጥንት ሆነው እያገለገሉ ነው። በጸጥታው ዘርፍ የተደረጉ ሪፎርሞች የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶች ትንኮሳን በብቃት መመከት የሚችል አቅም ፈጥረዋል።
በሌላ በኩል በዚህ ዘላቂ የሀገር ግንባታ ሒደት ውስጥ እንደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያሉ ተቋማት የሚጫወቱት ሚናም እጅግ የጎላ ነው። ነጻ እና ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ተቋም መገንባቱ፣ ሕዝቡ በነጻነት የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነቱን እንዲያረጋግጥ እና የሥልጣን ሽግግሮች ከጠብመንጃ እና ከሁከት ወጥተው በሰላማዊ የካርድ ድምፅ ብቻ እንዲወሰኑ ትልቅ መሠረት ጥሏል።
በተጨማሪም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለዘመናት የቆዩ መሠረታዊ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ወሳኝ ምሰሶ ሆኖ ምክረ ሐሳቦችን ማቅረብ ችሏል።
የሕዝብ ድምፅ በቀጥታ የሚንጸባረቅበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የመንግሥትን አሠራር በመቆጣጠር እና የተጠያቂነትን ሥርዓት በማስፈን ረገድ አቅሙን እያጎለበተ ነው።
በዚህም የተረጋጋ የፖለቲካ ሽግግርን ከማረጋገጥ አኳያ የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሒደት ለሀገረ መንግሥት ግንባታው ወሳኝ ምዕራፍ ሆኗል።
መምረጥ መብት ብቻ ሳይሆን የሀገርን ሕልውና የማስቀጠል፣ የተሻለ ፖሊሲ ያለውን አካል የመለየት እና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን የማረጋገጥ ግዴታም ጭምር በመሆኑ የእያንዳንዱ የዜጋ ድምፅ ሀገርን ከብተና የመታደግ እና የሥልጣን ፉክክር "ማን አሸነፈ?" ከሚለው ጠባብ አስተሳሰብ ወጥቶ "ሥርዓቱ እንዴት ይቀጥላል?" ወደሚለው መሠረታዊ ጥያቄ እንዲሸጋገር አድርጓል።
የአንድ ሀገር የፖለቲካ ብስለት እና የኢኮኖሚ ጥንካሬም የሚለካው በዘመናት መካከል ጸንተው በሚቆሙ ተቋሞቻቸው አቅም ነው። መሪዎች እና አስተዳደሮች የጊዜን ዑደት ተከትለው ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፤ ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማት ግን ትውልድን ተሻግረው የሀገረ መንግሥቱን ሕልውና በብቃት ያስቀጥላሉ።
ዛሬ እየተጣሉ ያሉ መዋቅራዊ መሠረቶች፣ ኢትዮጵያን ወደፊት ከሚገጥሟት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎች የሚታደጉ እና አጽንተው የሚያቆሙ የጸኑ አምዶች ናቸው።
በመሆኑም የሕግ የበላይነትን እና የሕዝብን ድምፅ የሚያስከብሩ ተቋማትን አቅም ቀጣይነት ባለው መልኩ በማጎልበት፣ በጽኑ አለት ላይ የቆመች ሀገርን ለትውልድ ማሻገር የዘመናችን ትልቁ የታሪክ አደራ ነው።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: