በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ የጎፋና የኦይዳ ህዝብ በጋራ የሚያከብሩት የዘመን መለወጫ በዓል "ጋዜ ማስቃላ" እና "ዮኦ ማስቃላ" በታላቅ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ይገኛል።
በዓሉ የአካባቢውን ህዝብ ማንነት፣ ጥንታዊ ታሪክና የቆየ የአብሮነት እሴት የሚያንፀባርቅ ሲሆን፤ በሁለቱም ብሔረሰቦች ባህልና ወግ መሰረት አዲስ ዓመትን በንፁህ ልብ መቀበል የህልውና መሰረት ተደርጎ ይታመናል።
ከእርድና ከደመራ ሥነ-ሥርዓት በፊት፣ በየአካባቢው የተፈጠሩ አለመግባባቶች፣ የተጣሉ ወገኖችና የቆዩ ቁርሾዎች በሀገር ሽማግሌዎች ጥረት ይፈታሉ።
በአዲሱ ዘመን ቂም እና በቀል ይዞ መሻገር እንደ ትልቅ ነውር ስለሚቆጠር፣ የጥላቻ ግንብ በፍቅርና በይቅርታ ይፈርሳል። ይህ የሰላም ሥርዓት በዓሉን ከባህላዊነቱ ባሻገር የሰው ልጅ የሞራል እሴቶች ማሳያ ያደርገዋል።
የጎፋ እና የኦይዳ ህዝብ በዓሉን ሲያከብሩ የይቅርታ ድልድይ በመገንባት፣ የጠፋን በማስታረቅ እና የተራራቁትን በማቀራረብ ነው።
በዚህ ወቅት የሚታየው የመተሳሰብና የመረዳዳት መንፈስ በዘመናት ውስጥ የቆዩትን ጠንካራ ማህበራዊ ትስስሮች የሚያድስ ሲሆን፤ በህዝቦች መካከል የተፈጠረውን የመቀራረብ ዕድል በመጠቀም መጪውን ጊዜ በፍቅርና በአንድነት ለመጀመር ታላቅ ጥረት ይደረጋል።
በሳውላ ከተማ እየተከበረ ባለው በዚህ የዘመን መለወጫ በዓል ላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአጎራባች ክልሎችና ዞኖች እንግዶች እንዲሁም የጎፋ እና ኦይዳ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።
ይህ የሰላም፣ የይቅርታ እና የአብሮነት መልዕክት ለቀጣዩ ትውልድ በቅብብሎሽ መተላለፉ ባህላዊ ሀብቶቻችንን ጠብቆ ለማቆየትና ህብረብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ ሚና ይጫወታል።
በአያንቱ እምሩ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: