Search

“ኢትዮጵያ የመሐል ሀገሩ ብቻ ሳትሆን የዳር ሀገሩም ሕዝቦቻችን መሆኗን ሀገራዊ ምክክሩ በተግባር አረጋግጧል”፡-ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

ሓሙስ መስከረም 14, 2019 116

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣ “ኢትዮጵያ የመሐል ሀገሩ ብቻ ሳትሆን የዳር ሀገሩም ሕዝቦቻችን መሆኗን ሀገራዊ ምክክሩ በተግባር አረጋግጧል” ሲሉ ተናገሩ።

ሀገራዊ ምክክሩ በታሪክ ታይቶ ባልታወቀ መልኩ በርካታ ተሳታፊዎችን ማካተቱ ለኢትዮጵያ ፈውስ እንጂ ሸክም ሆኖ አለማለፉንም ኮሚሽነሩ ከኢቢሲ ዶት ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል በተካሄደው ጉባኤ ከተለያዩ ክልሎች፣ ወረዳዎች፣ ከፌዴራል እንዲሁም በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተወጣጡ 4 ሺህ ሰዎች መሳተፋቸው ይታወሳል።

እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ገለጻ፣ በሀገራዊ ምክክሩ ቁጥሩ ከሚያስከትለው ተግዳሮት በላይ የኢትዮጵያ ሰላም በመብለጡ እና የሀገራችንን መጻኢ ዕድል ለመወሰን የሚያግዘን በመሆኑ፣ የሚከፈለው ዋጋ ተከፍሎ ተወካዮቹ በሚገባ ሐሳባቸውን እንዲያነሡ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

ኢትዮጵያውያን ተዋረዳዊ አወቃቀር ያለው ማኅበረሰብ ውጤት መሆናችንን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፣ በሕግና በባህል ደረጃ ትዕዛዝ ከላይ ወደ ታች እንደሚወርድ አስገንዝበዋል።

ምክክር ግን ከላይ ወደ ታች የሚወርድ ሳይሆን፣ አወያይ ወይም አመካካሪ ቁጭ ብሎ ሁለቱም ተወያይ ወገኖች ወደዚህ ምክክር ስንመጣ መግባባት ላይ እንደርሳለን ብለው የሚገናኙበት ሒደት መሆኑን አመላክተዋል።

በእኛ ነባራዊ ሁኔታ ያልተለመደው ይህ አካሄድ፣ በሀገራዊ ምክክር ሒደቱ በስኬት መተግበር የቻለ ጅምር መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የምክክር ሒደቱ ከመንግሥት፣ ከተሳታፊዎች እና ከተለያዩ አካላት ብዙ መሥዋዕትነትን የፈለገ እንደነበረም አስታውሰዋል።

ለምክክር ሒደቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ሁሉ ለማሟላት ወጪ ጠይቋል፤ በሒደቱ ከባድ የጤና እክል የገጠማቸው እና አደጋ ያጋጠማቸው ተሳታፊዎችም እንደነበሩ አንሥተዋል። የምክክሩ ተሳታፊ እናቶችም በተሳትፎ ላይ ሳሉ የአብራካቸውን ክፋይ ታቅፈዋል።

በዚህ ሁሉ ሒደት ግን 'በቃኝ፣ ይሄ በዛብኝ፣ ደከመኝ' ብለው ከመሄድ ይልቅ ተመካካሪዎች ቀን ከቀን ትሥሥራቸው እየጠበቀ ሲሄድ እንደነበር ፕሮፌሰር መስፍን አስረድተዋል።

‘እኛ በኢትዮጵያዊነታችን እንኮራለን፤ ኢትዮጵያዊነታችንን እንቀበላለን፤ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ለሁላችንም እኩል መሆን አለባት’ የሚል ሐሳብን ተሳታፊዎች ያነሡ እንደነበር እና በምክክር ሒደቱም የመሐል ሀገሩ ብቻ ሳይሆን የዳር ሀገሩም ሕዝቦቻችን ውክልና የታየበት መሆኑን አስታውሰዋል።

 

በዓይናለም ሃድራ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: