አለማችን በከፍተኛ ሙቀት፣ ድንገተኛ ጎርፍና የሰደድ እሳት ባሉ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች በሚፈተኑበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ተፈጥሮን መንከባከብና ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት የምኞት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ሆኗል፡፡
በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ውስጥ ፍፁም ተቃራኒ በሆነ መንገድ ከንግግር ይልቅ ተግባርን ያስቀደመው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሀገራችንን የማድረግ እምቅ አቅም፣ የፅናትና የአንድነት ታሪክ በተግባር ያስመሰከረ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ በመሆን ብቅ ብሏል።
በ2011 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት በመደመር እሳቤ የተቃኘው ይህ ጥረት ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ተጀመረ።
በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች እንዲተከሉ በማድረግ ሀገራዊ ለውጥን በተግባር እያሳየ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የአካባቢ መራቆትን፣ የደን መጨፍጨፍንና የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን በፅኑ መሰረት ለመፍታት ያለመ ነው።
ይህ ሰፊና የላቀ መርሃ ግብር ከዛፍ ተከላ መሰናዶ አልፎ የህዝብን የጋራ ህልምና ሀገራዊ ኩራት ያጎለበተ፣ ኢትዮጵያን ከአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በመከላከል ረገድ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ አርኣያ ያደረገ ታሪካዊ ሁነት ሆኖ ተመዝግቧል።
ኢትዮጵያውያን በቅርቡ በአንድ ጀምበር 805.3 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ያስመዘገቡት አስደናቂ ስኬት የቁጥር ብልጫን ብቻ ሳይሆን፣ የመንግስትና የህዝብ የተቀናጀ ሀገራዊ አቅም ማረጋገጫ ነው።
ይህ ክስተት ህዝብ ለአንድ በጎ ዓላማ በጋራ ሲቆም የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮችን እውን ማድረግ እንደሚችል እንደ ታሪካዊው የአድዋ ድልና የህዳሴ ግድብ ሁሉ "ብዙ ሆነው ሲገፉት ተራራም ይንቀሳቀሳል" የሚለውን ሀገራዊ ብሂል በተግባር ያረጋገጠ ነው።
ባለፉት ሰባት አመታት በተካሄደው ተግባር 54 ቢሊዮን ችግኞችን መሬት ማልበስ የተቻለ ሲሆን፣ ይህም የሀገራችንን የደን ሽፋን ከ17.2 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ ከፍ በማድረግ ተጨባጭ ጥቅም አስገኝቷል።
መርሃ ግብሩ ከችግኝ ተከላ ባሻገር የፍራፍሬ ዝርያዎች በስፋት እንዲለሙ በማድረግ የአርሶ አደሩን ህይወት በመቀየርና ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል።
ለጎረቤት ሀገራትም ችግኞችን በማካፈል የቀጣናውን አረንጓዴ ዲፕሎማሲ እውን ያደረገው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ ከዘመን አልፎ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር የአረንጓዴ ሀብት ተስፋ ለነገይቷ ሀገር ጠንካራ መሰረት ጥሏል።
ከተባበርን የማይቻል ነገር እንደሌለ ያስመሰከረው ይህ እንቅስቃሴ፣ ያንኑ የአንድነትና የትብብር መንፈስ በሌሎች ሀገራዊ የልማት ዘርፎች ላይ በመጠቀም ታሪክ መስራት እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት ሰጥቷል።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: