Search

የአንጋፋው ድምጻዊ ግርማ ነጋሽ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

ሓሙስ መስከረም 14, 2019 140
የአንጋፋው ድምጻዊ ግርማ ነጋሽ ሥርዓተ ቀብር በዛሬው ዕለት ቤተሰቦቹ፣ የሙያ አጋሮቹ፣ ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴደራል ተፈጽሟል።
ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ድምጻዊ ግርማ ነጋሽ፣ ለበርካታ የሙዚቃ አፍቃሪዎችና አድማጮች ፍቅርንና ትዝታን ያገነኑ ተወዳጅ ሥራዎችን አቅርቧል።
ከበርካታ የሙዚቃ ሥራዎቹ መካከል «ምነው ተለየሽኝ መስከረም ሳይጠባ» እና «እንገናኛለን» የሚሉት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በርካታ የማይረሱ ዜማዎችን ለሙዚቃ አፍቃሪዎች አበርክቷል።
አንጋፋው ከያኒ በፖሊስ ሠራዊት እና በብሔራዊ ቲያትር በድምጻዊነት ያገለገለ ሲሆን፤ በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ካስመዘገበው ስኬት ባሻገር በኢትዮጵያ ራዲዮ በሹፌርነትና በትራንስፖርት ስምሪት ክፍል ሠርቷል።
በተጨማሪም መሠረታቸው ከኢትዮጵያ ከሆኑና ከአንጋፋ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ባንዶች ጋር በታላላቅ መድረኮች ላይ ብቃቱን አስመስክሯል።
ሁልጊዜ ፈገግታ ከፊቱ እንደማይለይና ከሁሉ ጋር ተግባቢ እንደነበር የሚነገርለት ድምጻዊ ግርማ ነጋሽ፣ የሦስት ወንዶች እና የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበር።
በሀብታሙ ከበደ
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: