Search

የሕዝብ አለኝታ እና የጀግንነት ተምሳሌት፡- የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት

ሓሙስ መስከረም 14, 2019 145

ኢትዮጵያ በረጅም የታሪክ ጉዞዋ ሉዓላዊነቷን፣ ነፃነቷንና ሀገራዊ ማንነቷን አስጠብቃ የኖረች ሲሆን፤ ይህ የድልና የፅናት ጉዞ በወታደሮቿ የማይናወጥ መስዋዕትነት ተረጋግጧል።

ከውጭ ወራሪ ኃይሎች የሀገርን ዳር ድንበር ያስከበረው ያ የጀግንነት ታሪክ፣ ዛሬም የህዝብን ሰላም በመጠበቅና የሀገርን ህልውና በማስከበር ሂደት ውስጥ በፅናት ቀጥሏል።

ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎችና ማህበረሰቦች የተውጣጡ አባላት በጋራ የተሰለፉበት ይህ ታላቅ ተቋም፣ የሀገር ክብር፣ የህዝብ አለኝታና የትውልድ ተስፋ በመሆን የተጣለበትን ኃላፊነት በላቀ ብቃት በመወጣት ላይ ይገኛል።

ሠራዊቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በውጤታማነት የሚያከናውነው ከተገነባባቸው አራት ወርቃማ እሴቶች ማለትም ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር ከመሰለፍ፣ ምንጊዜም የተሟላ ስብዕናን ከመላበስ፣ ያልተሸራረፈ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብን ከመያዝ እና በማንኛውም ሁኔታ የላቀ ውጤት ከማስመዝገብ በመነሳት ነው።

ወታደራዊ ሕይወት የግል ምቾትን ከሀገር ጥቅም አስበልጦ አለማየት በመሆኑ፣ አባላቱ የቀኑን ሃሩርና የሌሊቱን ቁር ታግሰው ፈተናዎችን በፅናት በመሻገር ለተያዘው ዓላማ የቆሙ ክንደ-ብርቱዎች ናቸው።

ተቋሙ በትጥቅ ብቻ ሳይሆን በእውቀት፣ በሙያ፣ በሥነ-ምግባርና በተልዕኮ ታማኝነት በተገነባ ጠንካራ ስብዕና የሚመራ ሲሆን፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን የፅናት ዘብ ሆኖ የመጠበቅ መርሁን በጥብቅ ይከተላል።

የሠራዊቱ ዋነኛ የአሸናፊነት ምስጢርና የታላቅነቱ መሰረት ከሕዝብ ጋር ያለው ጥብቅ ትስስር ነው። ከህዝብ አብራክ የወጣው ይህ ኃይል፣ የህዝብ ፍቅርና አብሮነት ከታጠቀው ዘመናዊ መሳሪያ በላይ ግዙፍ አቅሙ እንደሆነ ያምናል፤ በችግር ጊዜ የሚደረግለት የሞራል ድጋፍም ውጣ ውረዶችን በብቃት እንዲሻገር ያስችለዋል።

ህዝብና ሠራዊት ፍፁም የማይነጣጠሉ በመሆናቸው፣ የሀሰት ፕሮፖጋንዳና የጥፋት ሴራ ይህንን ጠንካራ ቁርኝት ሊያዛባው አይችልም።

በተጨማሪም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ዘመኑ ያመጣውን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ልህቀት በመገንዘብ፣ ራሱን በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በዘመናዊ የውጊያ ብቃት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በሳይበር ደህንነት አቅም በማዘመን ላይ ይገኛል።

ይህ ዘመናዊነትና ጥንካሬ ከኮሪያና ኮንጎ ዘመቻዎች ጀምሮ በሱዳን አቢዬ፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ በተካሄዱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅናን ያተረፈ ታላቅ ዓለም አቀፋዊ ገፅታ አጎናጽፎታል። በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጊዜም ከህዝብ ጎን በመቆም ለቆመለት ዓላማ ታማኝነቱን አስመስክሯል።

መከላከያ ሠራዊት ወቅቶችና መንግሥታት ሲለዋወጡ በፅኑ መሰረት ላይ ቆሞ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር ገለልተኛና ታላቅ ተቋም ነው። ሀገርን ከምንም አስቀድሞ ሕይወቱን ለመክፈል የማይሳሳው ይህ አይበገሬ ሠራዊት፣ የትናንት ጀግኖች ወራሽ፣ የዛሬ የህዝብ አደራ ጠባቂና የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ ሆኖ ታሪካዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን ይቀጥላል።

 

በብሌን ደምበሎ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: