የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍትሐዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ባከናወነው ሰፊ ሥራ፣ የመስቀል በዓልን ለማክበር በዝግጅት ላይ በሚገኘው የጉራጌ ዞን፣ በእኖር እና እዣ ወረዳዎች የሚገኙ 19 የገጠር መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ አድርጓል።
የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታውን ለማከናወን ከ132 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን እና በዚህም 2 ሺህ 295 የሚጠጉ ቆጣሪዎች መገጠማቸውን አገልግሎቱ ገልጿል።
በአንድ ቆጣሪ አማካይ 5 የቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ቢሰላ፣ 11 ሺህ 475 ዜጎች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
ለዚህ የልማት ሥራ ስኬት 25.92 ኪሎ ሜትር መካከለኛ እና 38 ኪሎ ሜትር ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ አገልግሎቱ ለኢቢሲ በላከው መረጃ አስታውቋል።
ፕሮጀክቱን ከማስፈጸም ባለፈ፣ ከወጣው አጠቃላይ ወጪ 40 ሚሊዮን ብር የሚሆነው በኅብረተሰቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ እና የባለቤትነት ስሜት የተሸፈነ መሆኑ የሕዝብ እና የተቋሙን አብሮነት ድንቅ ማሳያ እንደሆነ ነው የገለጸው።
ይህ የልማት ሥራ የአካባቢውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማነቃቃት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። የልማት ሥራው የአካባቢውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማሳደጉም በላይ፣ የዘንድሮውን የመስቀል በዓል ለነዋሪዎች ልዩ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: