የዓለምአቀፉን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አቅጣጫ የሚወስነው የአሜሪካ እና የቻይና ዲፕሎማሲያዊ ፍጭት አዲስ ምዕራፍ እየያዘ ይመስላል።
በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የታሪካዊው የመሪዎች ስብሰባ፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ በሁለቱ የበላይ ኃያላን ሀገራት መካከል ያለውን የከረረ ውጥረት ለማረጋጋት ተገናኝተው መክረዋል።
ሁለቱ መሪዎች የነጠሩ ስልታዊ ልዩነቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ ባይፈቱም፣ በዓለም አቀፍ የኃይል ሚዛን እና በኢኮኖሚ ቀውስ ዙሪያ ግልጽ የሆኑ አቋሞችን ማንፀባረቃቸው ተመልክቷል።
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ የቤጂንግን መሠረታዊ የፖለቲካ መስመር በግልጽ ያስመሩበት ሲሆን ሁለቱ ሀገራት በእድገት ላይ ያለ ኃይል እና ነባር ኃያል ሀገር ወደ ከፋ ግጭት የሚያመሩበትን ወጥመድ ማስወገድ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የሁለቱ ግዙፍ ሀገራት ውድድር አንዱ አሸንፎ ሌላው የሚወድቅበት የሞት ሽረት ትግል ሳይሆን ወሰኑን የጠበቀ ጤናማ የዕድገት ፉክክር ሊሆን እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከቻይና ጋር ያለውን የንግድ እና የኢኮኖሚ ፍጭት ለማቃለል ፍላጎት እንዳላቸው በመግለጽ፣ በመከባበር ላይ የተመሠረተ የስልታዊ ንግግር አስፈላጊነትን አንስተዋል።
ሆኖም የታይዋን ጉዳይ በዋሽንግተን እና በቤጂንግ መካከል ዋነኛው የጂኦ-ፖለቲካ ቀይ መስመር ሆኖ ቀጥሏል። ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ለትራምፕ ባስተላለፉት ቀጥተኛና መልዕክት አሜሪካ የታይዋንን ነጻነት የመደገፍ ፍላጎትን እንድትቃወም እና ጉዳዩን በጥንቃቄ እንድትይዘው አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለታይዋን ይላክ የነበረውን የ14 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ፓኬጅ ማዘገየታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ይህንን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ከቻይና ጋር ለሚደረግ የንግድ ድርድር እንደ ማደራደሪያ ካርድ የመጠቀም ስልታቸው ደግሞ በዋሽንግተን የፖለቲካ ክበቦች ዘንድ ትልቅ አከራካሪ አጀንዳ ሆኗል።
በሌላ በኩል በመካከለኛው ምስራቅ የሚታየው የጦርነት ስጋት እና የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ እና የኃይል አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።
አሜሪካ ቻይና የቴህራንን ኢኮኖሚ በማግለል ረገድ አብራ እንድትሰለፍ ብትፈልግም፣ የኢራን ትልቋ የንግድ አጋር የሆነችው ቻይና ግን በዚህ ውጥረት ውስጥ በቀጥታ ከመግባት ተቆጥባለች።
ፕሬዝዳንት ሺ ሁለቱም ወገኖች ወደ ቀደመው ጊዜያዊ የሰላም ስምምነት እንዲመለሱ ድጋፋቸውን ከመግለጽ ውጭ በጉዳዩ ላይ አዲስ ስምምነት አልተደረሰም።
ይህ በኋይት ሀውስ የተከናወነው የዲፕሎማሲ ትዕይንት በአሜሪካ ህግ አውጪዎች ዘንድ የተለያየ ምላሽ አስተናግዷል። የተወሰኑ ሴናተሮች አሜሪካ ከቻይና ጋር ያሏት መሠረታዊ አለመግባባቶች ሳይፈቱ እንዲህ ዓይነቱ አቀባበል መደረጉን ሲተቹ፣ ሌሎች ደግሞ ከውጥረት ይልቅ ውይይት የከፋ ግጭትን ለማስወገድ ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ደግፈውታል።
የሁለቱ ግዙፍ ሀገራት መሪዎች ስብሰባ በኢኮኖሚና በፖለቲካው ዘርፍ ያሉ መሠረታዊ ልዩነቶችን ሙሉ በሙሉ ባይፈታም፣ በሁለቱ ኃያላን መካከል ሊከሰት የሚችለውን ቀጥተኛ ግጭት ለመግታት እና ዓለም አቀፍ ስጋቶችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማረጋጋት ትልቅ ትርጉም ያለው እርምጃ መሆኑን የጂኦ-ፖለቲካ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: