Search

የጋራ እሴቶቻችን ለጽኑ አንድነት፡ ከትናንት አብሮነት እስከ ነገ ሀገር ግንባታ

ዓርብ መስከረም 15, 2019 137

ሀገር በቀል እሴቶች ኢትዮጵያውያን ከዘመናት ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ተሞክሮዎቻቸው ያፈሯቸው የሞራል፣ የሥነ ምግባር እና የአብሮነት መርሆች ናቸው።

እነዚህ እሴቶች የማኅበረሰቡን ማንነት ከማንጸባረቅ ባለፈ ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስርን በመፍጠር ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት እና ጽኑ ሀገረ መንግሥት በመገንባት ረገድ ያላቸው ፋይዳ እጅግ የላቀ ነው።

ዘርፈ ብዙ ቋንቋዎችን፣ ሕዝቦችን እና ባህሎችን ያቀፈችው ኢትዮጵያ የበለጸጉ ሀገር በቀል የዕውቀት እና የጥበብ ተሞክሮዎች ባለቤት ናት።

ኢትዮጵያ ዘመናትን ተሻግራ፣ ውጣ ውረዶችን አልፋ ጸንታ እንድትቆም ያስቻላት ዋናው ምሰሶ ዜጎቿ የገነቡት የጋራ መከባበር፣ ፍቅር፣ መቻቻል እና ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር ነው።

በሀገራችን ያሉ ብዝኃነቶች የመከፋፈያ መንስኤዎች ሳይሆኑ ማኅበራዊ ኅብረ ቀለማችንን የሚያጎለብቱ እና አንዱ ከሌላው የሚማርባቸው የባህል ሃብቶቻችን ናቸው።

በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ጎልተው የሚታዩት የእርስ በርስ መደጋገፍ እና መረዳዳት ሥርዓቶች ማኅበረሰባችንን በፍቅር እና በአንድነት አቆይተውታል።

እድር፣ እቁብ፣ ማኅበር እና ደቦ (ጅጊ) ሕዝቡ ደስታውንም ሆነ ሃዘኑን በጋራ የሚካፈልባቸው፤ እንዲሁም የኢኮኖሚ አቅሙን የሚያጎለብትባቸው ማኅበራዊ ምሰሶዎች ናቸው።

በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ ሀገር በቀል የዕርቅ ሥርዓቶች ደግሞ ፍትህን በሰላም በማስፈን ረገድ የማይተካ ሚና አላቸው።

የገዳ ሥርዓት የዲሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት አከባበር እና የሰላም መገለጫ ከመሆን ባለፈ፤ ግጭቶችን በግልጽነት እና በፍትሃዊነት የሚፈታ ትልቅ የአስተዳደር ማዕቀፍ ነው።

በተመሳሳይ በስፋት የሚታወቀው የሽምግልና ሥርዓት በሀገር ሽማግሌዎች እና በሃይማኖት አባቶች አማካኝነት የሚደረግ የዕርቅ መንገድ ነው።

ይህ አኩሪ ባህል የሲዳማው "አፊኒ"፣ የአፋሩ "መዓዳ"፣ የሶማሌው "ሄር ኢሴ"፣ የጉራጌው "የጆካ"፣ የኦሮሞው "ጉማ" እና ሌሎችም በርካታ የዕርቅ ሥርዓቶችን በውስጡ የያዘ ነው።

እነዚህ ሥርዓቶች የጠላትነትን ግድግዳ በማፍረስ ፍቅርን የሚመልሱ እንዲሁም ጉዳዮችን ያለፍርድ ቤት ውጣ ውረድ በመፍታት ሕግ እና ሥርዓት እንዲከበር ጠንካራ ዋስትና የሚሰጡ ናቸው።

ከማንኛውም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም በተሻለ መልኩ ሕዝቦችን በሥነ ልቦና ማሰር የሚችሉት እነዚህ ሀገር በቀል እሴቶች ናቸው።

ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች እና ሥልጣኖች ሊለዋወጡ ይችላሉ፤ ነገር ግን በማኅበረሰብ፣ በታሪክ እና በባህል ትስስር ላይ የተመሰረቱት እሴቶች ለሰላም እና ለዘላቂ አንድነት የማይናወጥ መሠረት ይሰጣሉ።

ዜጎች በባህላቸው፣ በእምነታቸው እና በማኅበራዊ መርሆቻቸው ሲተሳሰሩ ሉዓላዊነትን እና አንድነትን ለማስጠበቅ የሚደረገው ጥረት ከልብ የመነጨ ይሆናል።

የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም፣ ዕድገት እና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ እውን ለማድረግ ከውጭ ከሚመጡ አስተሳሰቦች ይልቅ የራሳችንን ሀገር በቀል እሴቶች ማዕከል ማድረግ ይገባናል።

በተለይም አጀንዳዎችን በማሰባሰብ እና ዋናውን የምክክር ጉባኤ አካሂዶ ምክረ ሀሳቦችን ባጠናቀቀው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ውስጥ እነዚህ ማኅበራዊ ጸጋዎች እንደ ማዕዘን ድንጋይ አገልግለዋል።

በምክክር ሂደቱ ውስጥ ልዩነቶችን እንደ ሃብት በመቁጠር በአብሮነት የመኖርን መንፈስ ማጠናከር የተቻለው በእነዚህ እሴቶቻችን ነው።

በመሆኑም እነዚህን ውድ የሰላም እና የአብሮነት እሴቶች ከመንከባከብ ባለፈ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር በማዋሃድ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይኖርብናል።

ይህን ስናደርግ ሰላሟ የሰፈነ፣ የተከበረች እና በጽኑ መሠረት ላይ የቆመች ኢትዮጵያን መገንባት እንችላለን።

በሜሮን ንብረት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: