በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ውስጥ የጀርባ አጥንት የሆነው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ በመደመር መንግሥት በተከተለው መዋቅራዊ የፖሊሲ ማሻሻያ እና የተቀናጀ አሰራር ምክንያት አዲስ የስኬት ምዕራፍ ውስጥ ይገኛል።
ቀደም ሲል በፋይናንስ እጥረትና በምርታማነት ውድቀት ተስፋ ቆርጠው የነበሩ ፋብሪካዎች፣ ዛሬ በፅኑ መሠረት ላይ በመቆም ሙሉ አቅማቸውን ወደ ማውጣት ተሸጋግረዋል።
ይህ ውጤት ተኮር አካሄድ ዘርፉን ከነበረበት የቀዘቀዘ እንቅስቃሴ በመታደግ የኢትዮጵያን የመቻል አቅምና የኢኮኖሚ እድገት በዋናነት እንዲመራ አስችሎታል።
ቀደም ባሉት ዓመታት ከ30 እስከ 40 በመቶ ዝቅ ብሎ የነበረው የአምራች ኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት አቅም በአሁኑ ወቅት ወደ 67 በመቶ ከፍ ማለቱ የኢትዮጵያን አዲስ የከፍታ ጉዞ የሚያረጋግጥ ቁልፍ ማረጋገጫ ሆኗል።
ይህንን እመርታዊ ስኬት ለማስመዝገብ ደግሞ ለዘርፉ ትልቅ ፈተና የነበረውን የፋይናንስ ማነቆ የመፍታት እርምጃ ተወስዷል።
ቀደም ሲል ለኢንዱስትሪዎች ይሰጥ የነበረው 40 ቢሊዮን ብር የብድር መጠን ወደ 115 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ በመደረጉ፣ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ፣ ተወዳዳሪና ትርፋማ እንዲሆኑ ትልቅ የፋይናንስ ጉልበት ሆኗቸዋል።
በዚህ የተነሳ የሀገር ውስጥ ምርትን በማስፋፋት እና የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ከ2 ሺህ 800 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ የተቻለ ሲሆን፣ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል።
እነዚህ የመንግሥት የፖሊሲ ውሳኔዎች የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሀገራችንን የንግድ ሚዛን እንዲያስተካክል ዘላቂ ተወዳዳሪነትን እንዲያረጋግጥ እና የኢትዮጵያን አይበገሬ የምርታማነት አቅም ለዓለም እንዲያሳይ መንገድ ከፍተዋል።
በውጤት ተኮር አመራር የተገነባው ይህ ጠንካራ መሠረት በተያዘው የበጀት ዓመት ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ለተያዘው ትልቅ ሀገራዊ ዕቅድ ስኬት አስተማማኝ ዋስትና ሆኗል።
የመደመር መንግሥት የወሰዳቸው የፖሊሲ እርምጃዎችም የኢንዱስትሪ ዘርፉን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባትና ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: