የአንድ ሀገር አጠቃላይ ልዕልና እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚረጋገጠው በጠንካራ ወታደራዊ አቅም፣ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ፣ በድርድር ብቃት እና በዓለም አቀፍ ምህዳር በሚፈጠር ስትራቴጂያዊ ተደማጭነት ነው።
በምሥራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ ጉልህ የጂኦ-ፖለቲካዊ ሚና ያላት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተገበረችው ያለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሁለንተናዊ አቅሟን በተግባር ያረጋገጠችበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ይህ ስኬት በወታደራዊ በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ከተመዘገቡት እመርታዎች ባሻገር በዓለም አቀፍ የድርድር መድረኮች ላይ ጎልቶ እየታየ ነው።
በተለይም ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) ጥምረት አባል ሆና መቀላቀሏ እና በመድረኩ እያሳየችው ያለው ንቁ ተሳትፎ የውጭ ግንኙነቷን ወደ አዲስ ከፍታ ያሸጋገረ የዲፕሎማሲ ድል ነው።
በዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ሚዛን ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው አዳጊ እና ኃያላን መንግሥታት ጋር በእኩልነት እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርታ መሥራቷ የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ድምፅ በከፍተኛ ደረጃ ከፍ አድርጎታል።
በብሪክስ መድረክ ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለው አፈጻጸም በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በመሠረተ ልማት ዝርጋታ መስኮች ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ ሳትሰጥ ጠንካራ ድርድር የማድረግ ብቃቷን አሳይቷል።
ከዚህም አልፎ የአዳጊ መንግሥታትን ጥቅም በማስጠበቅ እና የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ተቋማት አሠራር ፍትሐዊ እንዲሆን በመጠየቅ ረገድ የአፍሪካ አህጉር አንደበተ ርዕቱ በመሆን የሞጋችነት ሚናዋን በተግባር አረጋግጣለች።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የምትጫወተው ሚና በቀላሉ የሚተካ አይደለም። በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን የከፈለችው ውድ ዋጋ የሽብርተኝነትን መስፋፋት ለመግታት ያደረገችው ተጋድሎ እንዲሁም የኃይል አቅርቦትን መሠረት ያደረገው የመሠረተ ልማት ትስስር በቀጣናው ያላትን የጎላ ክብር በከፍተኛ ደረጃ አዝልቆታል።
በየጊዜው እያደገ የመጣው አጠቃላይ አቅሟ እና ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ስኬቷ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ አይቀሬ ተጽዕኖ ፈጣሪ አድርጓታል።
በብሪክስ የታየው አፈጻጸም በቀጣናው ያላት የጎላ ሚና እና እያደገ የመጣው ተደማጭነቷ፤ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ጉዞ ማንም ሊገታው እንደማይችል ግልጽ ማረጋገጫ ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: