ከጅቡቲ ዳመርጆግ እስከ ኢትዮጵያ ደወሌ የሚዘረጋው የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር፣ የነዳጅ አቅርቦት ሂደትን በማቀላጠፍ የሎጂስቲክስ ወጪን እና የመጓጓዣ መዘግየትን ለመቀነስ የሚያስችል ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የቧንቧ መስመሩ መገንባት፣ አላስፈላጊ ብልሹ አሠራሮችን፣ የመጓጓዣ መዘግየቶችንና በመንገድ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የነዳጅ ብክነቶችን በማስቀረት፣ የነዳጅ ማጓጓዣ ሥርዓቱን ይበልጥ ቀልጣፋና አስተማማኝ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።
120 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በዳንጎቴ ግሩፕ የጋራ ሽርክና የሚገነባ ነው።
ለፕሮጀክቱ ማፈጸሚያ የመጀመሪያ የወጪ ግምት 660 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተያዘለት ሲሆን፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባ መታቀዱንም ሃላፊው ተናግረዋል።
ሌላው የፕሮጀክቱ አካል ከፍተኛ አቅም ያላቸው የነዳጅ ማከማቻ ዴፖዎችን መገንባት እንደሆነ ያነሱት ዶ/ር ብሩክ፣ በጅቡቲ ዳመርጆግ የሚገነባውና እስከ 375 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ነዳጅ የመያዝ አቅም የሚኖረው ዴፖ፣ ነዳጅ ከመርከብ በፍጥነት ለማራገፍና በመርከቦች መዘግየት ምክንያት የሚወጣውን ተጨማሪ ወጪ ለማስቀረት ያስችላል ብለዋል።
በተመሳሳይ አቅም በደወሌ የሚገነባው ሁለተኛው ዴፖ ደግሞ ነዳጅን በስትራቴጂካዊ ደረጃ ለማከማቸት ከመጠቀሙ ባሻገር፣ ከጅቡቲ በቧንቧ የሚመጣውን ነዳጅ ወደ ተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለማሰራጨት እንደሚያገለግልም ነው የገለጹት።
በተለይም የደወሌው ዴፖ ከኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ጋር የሚገናኝ በመሆኑ፣ ነዳጅን በቦቴ መኪናዎች ብቻ ሳይሆን በባቡርም ጭምር ለማጓጓዝ የሚያስችል ተጨማሪ የሎጂስቲክስ አማራጭ እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
ዶ/ር ብሩክ፣ ነዳጅን ከቦቴ መኪና ማጓጓዣ ወደ ቧንቧ መስመር ማሸጋገር፣ በመጓጓዣ ሰንሰለቱ ውስጥ የሚከሰቱ አላስፈላጊ ንክኪዎችን፣ የጊዜ ብክነትንና ወጪን በመቀነስ በኢኮኖሚው ላይ ተጨማሪ ውጤታማነት ሊያመጣ እንደሚችል ገልጸዋል።
የዳመርጆግ–ደወሌ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር፣ የነዳጅ ማጓጓዣ ሂደቱን ከማቀላጠፍ ባለፈ በጅቡቲ እና ኢትዮጵያ የንግድ ሎጂስቲክስ ሰንሰለት ውስጥ ያለውን የጊዜና የወጪ ጫና ለመቀነስ አዲስ አቅም እንደሚፈጥርም ሃላፊው አንስተዋል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: