በአፍሪካ ሁለተኛው ከፍተኛ ቁጥር የሆነ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዕድገቷ ወደፊት እየተራመደች ባለችበት በዚህ ወቅት፣ የባሕር በር ጉዳይ ከንግድ በላይ የስትራቴጂክ ጉዳይ ነው።
የባሕር በር አማራጭ መኖሩ ለውጭ ንግድ፣ ለሎጂስቲክስ፣ ለኢኮኖሚ ትሥሥር እና ለቀጣናዊ ትብብር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል።
የኪንግ ኦፍ ዓባይ መሥራች እና ባለቤት የሆኑት ኡስታዝ ጀማል በሽር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ከቀይ ባሕር ጋር ጠንካራ ግንኙነት ነበራት።
በተለያዩ ወቅቶች በበርበራ፣ በአሰብ እና በምጽዋ አካባቢ ያሉ ወደቦችን ትጠቀም እንደነበር እና በ1950ዎቹም ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ኮሌጅ በማቋቋም ከተለያዩ ሀገራት ጋር ልምድ እና ዕውቀት ስትለዋወጥ መቆየቷን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ከባሕር በር መለየት በተለያዩ ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ሒደቶች የተፈጠረ ሁኔታ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህም በውጭ ንግድ እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ፈጥሯል ብለዋል። በተለይም የኤርትራ መገንጠል ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር የበለጠ ያራቀ ታሪካዊ ሒደት መሆኑን ነው ያነሡት።
የባሕር በር ጉዳይ የሌላ ሀገርን ሉዓላዊነት መጋፋት ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያ የንግድ እና የሎጂስቲክስ አማራጮችን ማስፋት መሆኑን የገለጹት ኡስታዝ ጀማል በሽር፣ በተለይም የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ እና የኢኮኖሚ አቅም ከቀጣናው የወደብ እና የንግድ ኮሪደሮች ጋር ቢገናኝ ለቀጣናው ኢኮኖሚ አዳዲስ ዕድሎችን ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል።
የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር አደም ካሚል በበኩላቸው፣ ቀይ ባሕር ከኢትዮጵያ ታሪክ እና ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ገልጸዋል።
የአክሱም መንግሥት በቀይ ባሕር ዙሪያ ከነበሩ ኃያላን መንግሥታት መካከል አንዱ እንደነበር ጠቅሰው፣ የንግድ እና የባሕር መስመሮች በአክሱም ሥልጣኔ ውስጥ የነበራቸውን ከፍተኛ ሚና አንስተዋል።
የቀይ ባሕር ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ በአሁኑ ወቅት እየጎላ መምጣቱን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ከቀጣናው የባሕር እና የንግድ ትሥሥር ጋር ያላትን ግንኙነት በአዲስ መልክ ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይን እውን ለማድረግ ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት በማድረግ የጋራ አቅምን ማሰባሰብ እንደሚገባ ኡስታዝ ጀማል በሽር ጠቁመዋል። በታሪክ ውስጥም የውጭ ጫናዎችን ለመመከት ኢትዮጵያውያን የጋራ ጉዳይን በማስቀደም አብረው የቆሙባቸው ምሳሌዎች እንዳሉ አስታውሰዋል።
የባሕር በር ጉዳይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ከቀይ ባሕር፣ ከአፍሪካ ቀንድ ንግድ፣ ከወደብ ልማት፣ ከመጓጓዣ እና ከቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትሥሥር ጋር የሚያያዝ መሆኑ ተጠቁሟል።
በመሆኑም ጉዳዩ የኢትዮጵያን ጥቅም ከጎረቤት ሀገራት ሉዓላዊነት እና ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር በማጣጣም በዲፕሎማሲ እና በሰላማዊ ድርድር መፍታት እንደሚቻል ተገልጿል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: