Search

የተግባር ዘመን፡ የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍሬ

ዓርብ መስከረም 15, 2019 202

ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች፣ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከ10 ሺሕ በላይ ዕጩዎች የተሳተፉበትን 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በስኬት ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያ፣ አዲስ የመንግሥት ምሥረታ ዋዜማ ላይ ትገኛለች።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ሰሞኑን እንዳስታወቁት፣ አዲሱ መንግሥት የሚዋቀርበትና የፓርላማ አባላት ቃለ-መሐላ የሚፈጽሙበት ሥነ-ሥርዓት ዝግጅት ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል።

ይህ ታሪካዊ የሥልጣን ሽግግር የሕዝብ ድምፅ ወደ ተጨባጭ አስተዳደር የሚቀየርበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው።

በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 58(2) መሠረት፣ አዲስ የተመረጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመኑን የሚጀምረው ከመስከረም ወር መጨረሻ ሳምንት የመጀመሪያው ሰኞ በመሆኑ፤ የፓርላማው መከፈቻ እና የፌዴራል አስፈጻሚ አካሉ ምሥረታ መስከረም 25 ቀን ይከናወናል።

በተጓዳኝም በአንቀጽ 56 ድንጋጌ መሠረት በምርጫው አብላጫውን ድምፅ ያገኘው ገዢው የብልጽግና ፓርቲ መንግሥትን የማዋቀር እና የመምራት ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ይረከባል።

ይህ አዲስ የሥራ ዘመን መንግሥት የሕዝብን አደራ ተቀብሎ የገባውን ቃል ኪዳን ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀይርበት መድረክ ነው።

ዜጎች በምርጫ የሰጡት ውክልና ሰፊው የመደመር እሳቤ ተቋማዊ ሆኖ ከዚህ ቀደም የተጀመሩ የመሠረተ ልማት፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የሰላም ግንባታ ሥራዎች ሳይቋረጡ በተጠናከረ ፍጥነት እንዲቀጥሉ ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ነው።

በመሆኑም መጪዎቹ አምስት ዓመታት አዲሱ መንግሥት ማኅበራዊ ትስስርን በማጽናት እና ዜጎች የሚኮሩበትን ኢኮኖሚያዊ ውጤት በማምጣት የተግባር ፈተናውን የሚያልፍበት ዘመን ይሆናል።

የምርጫው ሂደት አሁን ወደ ጠንካራ የሥራ ምዕራፍ የተሸጋገረ ሲሆን፤ የኢትዮጵያውያን እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዐይኖች ሕገ-መንግሥታዊ ቃሉን ጠብቆ የዜጎችን የተሻለ ነገ ዕውን ወደሚያደርገው አዲስ አስተዳደር አቅጣጫ አተኩረዋል።

በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: