ኢትዮጵያ የዘመናት ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ሕመሞቿን በራሷ ልጆች ጥበብ ለማከም ባቋቋመችው ሀገራዊ የምክክር መድረክ አማካኝነት ለችግሮቿ ዘላቂ መፍትሔ አቅጣጫ እያስቀመጠች ትገኛለች።
ትናንት የነበራትን የችግር እና የተረጂነት ስም ዛሬ ላይ በጠንካራ የሥራ ባህል በመቀየር፣ በዓለም አቀፉ መድረክ ያላትን ተሰሚነት እና ስትራቴጂካዊ አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሳድጋለች።
የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና የውስጥ ፈተናዎች ቢያጋጥሟትም፣ ከጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ዝንፍ ሳትል ራዕይዋን ወደ መሬት በማውረድ ላይ ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንደሚያነሱት ኢትዮጵያ በሥራ ላይ ናት፤ የተጀመረውን የለውጥ ግስጋሴ ወደ ኋላ የመመለስ ዕድል የለም።
ይህ እውነታ በቃላት ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን፣ በመላው ኢትዮጵያ እየተከናወኑ ባሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተግባር እየተረጋገጠ ይገኛል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬታማ ግንባታ፣ የከተሞችን መልክ እየቀየሩ ያሉ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች፣ በቅርቡ ይፋ የተደረገው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ ሜጋ ኤርፖርት ግንባታ እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አቅም የፈጠሩት አጠቃላይ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የዚህ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ህያው ማሳያዎች ናቸው።
እነዚህ ግዙፍ የልማት ውጥኖች የከተሞችን ውበት እና ምቹነት ከመጨመራቸውም ባሻገር ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት በማሻሻል ብሩህ ተስፋን ፈንጥቀዋል።
ከእነዚህ ታሪካዊ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገቷን ለማረጋገጥ ከአጋሮቿ ጋር በመሆን ግዙፍ የነዳጅ ማጓጓዣ ፓይፕላይን እና የማከማቻ ፕሮጀክትን ይፋ አድርጋለች።
በጅቡቲ ዳመርጆግ እና በኢትዮጵያ ደወሌ መካከል የሚዘረጋው ይህ የ120 ኪሎ ሜትር የነዳጅ ማጓጓዣ መሠረተ ልማት በሁለቱም በኩል በድምሩ ከ1 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የመያዝ አቅም ያላቸው የነዳጅ ማከማቻዎችን ያካተተ ነው።
የዚህ ፕሮጀክት ትልቁ ፋይዳ ነዳጅ በቦቴ ተጭኖ አዲስ አበባ ለመድረስ የሚወስደውን የ5 ቀን አድካሚ ጉዞ ወደ 1 ቀን ዝቅ ማድረጉ ብቻ አይደለም።
የንግድ፣ የኢንዱስትሪ እና የትራንስፖርት ወጪዎችን በከፍተኛ ደረጃ ከመቀነሱም በላይ፣ በነዳጅ ማጓጓዣ ላይ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያድናል፤ የከባድ መኪኖች ምልልስ በመቀነሱም የመንገድ መሠረተ ልማትን ከብልሽት ይታደጋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ በቀይ ባሕር አካባቢ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊከሰቱ የሚችሉ የደኅንነት አለመረጋጋቶችን ታሳቢ በማድረግ፣ የኢትዮጵያን የነዳጅ ክምችት አስተማማኝ በማድረግ ዘላቂ የኃይል አቅርቦት ሉዓላዊነትን ያረጋግጣል።
ይህ ስትራቴጂያዊ እርምጃ በማንኛውም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ እና በየትኛውም ወቅት ኢትዮጵያ የልማት ትኩረቷን እንደማትስት የሚያሳይ ትልቅ ማረጋገጫ ነው።
ከጀመረችው የመታደስ እና የብልጽግና ጉዞ የሚያስቀራት አንዳችም ኃይል እንደሌለ እና የልማት መንኮራኩሯ እንደማይገታ ለዓለም እያሳየች ነው።
በርግጥም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት “ኢትዮጵያ ትጸናለች! ኢትዮጵያ ትሸጋገራለች! ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች! እንደለመደችው ደጋግማ ፈተናዎችን እያሸነፈች ወደ ግቧ ትገሰግሳለች! የሚያቆማትም ምንም ኃይል የለም!”
በዓይናለም ሃድራ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: