Search

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሽግግር፡ ወደ ሰላማዊ ውይይት እና አካታች ዴሞክራሲ

ዓርብ መስከረም 15, 2019 90

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሳትፎ እና የሕዝብ አካታችነት ጉዞ ባለፉት ስምንት ዓመታት ፈተናዎችን አልፎ ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግቦበታል።

ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መኖሪያ እንደመሆኗ መጠን የፖለቲካ አካታችነት ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ እና ለዘላቂ ልማት ወሳኝ ምሰሶ ነው።

የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ ቋንቋቸውን የመጠቀም እና በፌዴራል መንግሥት ሥልጣን አወቃቀር ላይ የመሳተፍ መብት ዋስትና ቢሰጥም ባለፉት ሥርዓቶች ከወረቀት ባለፈ መሬት ላይ የወረደ እና እውነተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የታከለበት አሠራር በበቂ ሁኔታ አልታየም።

በቅርብ ዓመታት በኢትዮጵያ የተካሄደውን የለውጥ ሂደት ተከትሎ ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በነፃነት የሚወያዩበት እና መግባባት የሚፈጥሩበት ሰፊ መድረክ ተፈጥሯል።

ለዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ፖለቲካዊ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲገቡ መደረጉ የፖለቲካውን ምህዳር ይበልጥ አሳታፊ አድርጎታል።

ይህን በጎ ጅምር ተቋማዊ ለማድረግ የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሄደበት የአጀንዳ ማሰባሰብ እና አጀንዳዎችን ወደ ፖሊሲ ምክረ ሀሳብ የማሳደግ የተሳካ ሂደት የዚሁ ማሳያ ናቸው።

ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎችን ያካተቱት እነዚህ መድረኮች ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ባህልን አዳብረዋል።

በተለይም እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በተካሄደው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ላይ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሰባሰቡ ተሳታፊዎች በሰፊው መክረዋል።

በዚሁ ሂደት በዋናው ጉባኤ ተጨምቀው ከቀረቡት 400 አጀንዳዎች መካከል በ396ቱ ላይ ሰፊ መግባባት ተደርሶ የጋራ ምክረ ሀሳብ ሊቀመጥላቸው ችሏል።

በተጓዳኝም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲስ መዋቅር እና አመራር ተደራጅቶ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር በተለየ ነጻነትን እና ተአማኒነትን ለማረጋገጥ ያደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው።

በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት መሳተፍ መቻላቸው የፖለቲካ ተሳትፎ ማለት ድምጽ መስጠት ብቻ ሳይሆን ሀገርን በመገንባት ሂደት ውስጥ የውሳኔ ሰጪነት ባለቤት መሆን መሆኑን አረጋግጧል።

ይህ አካታችነት በተለይ ሴቶች፣ ወጣቶች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በፖለቲካው ማዕቀፍ ውስጥ ንቁ ተዋናይ እንዲሆኑ በሮችን ከፍቷል።

አሁንም ጅምሩን መሰረት ለማስያዝ የፖለቲካ ጽንፈኝነት የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሽግግር ፈተና ውስጥ የሚከትት በመሆኑ ቀጣይነት ያለው የልሂቃን እና የሕዝብ ውይይት ወሳኝ ነው።

ባለፉት ዓመታት የፖለቲካ ተሳትፎን ከማሳደግ አንፃር የተከናወኑት ተግባራት በተለይ ለዲጂታል ትውልዱ ትልቅ መሰረት የጣሉ ናቸው።

እንደ ፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ እና ቴሌብር ያሉ አዳዲስ ዲጂታል መድረኮች ዜጎች ከፖለቲካው እና ከኢኮኖሚው ሥርዓት ጋር ይበልጥ እንዲተሳሰሩ እና ሰፊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መንገድ ከፍተዋል።

ልዩነቶችን በውይይት እየፈቱ፣ ሰፊውን ህብረተሰብ ያካተተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት የሁላችንንም የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ የዘመናችን ትልቁ የቤት ስራ ነው።

በሜሮን ንብረት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: