Search

"ወደ ውስጥ መመልከት" ፡ ሀገር በቀል እሴቶቻችን የኢትዮጵያ ከፍታ መሰረቶች

ዓርብ መስከረም 15, 2019 78

ታሪክን ከትውልድ ትውልድ አሻግሮ፣ ማዕበልን ችሎ የክብር እና የሉዓላዊነት ባለቤት መሆን ቀላል አይደለም።

ኢትዮጵያ በተለያዩ የጂኦፖለቲካዊ ጫናዎች እና የዘመናት ውጣ ውረዶች መሀል አልፋ የዛሬ ማንነቷን የጨበጠችው በውጭ ኃይሎች መነጽር ወይም በተኮረጁ ርዕዮተ ዓለማት አይደለም።

ይልቁንም በሕዝቧ ውስጥ ባሉ እንዲሁም በዘመናት ተፈትነው ባለፉ ጥንታዊ እና ጽኑ ሀገር በቀል እሴቶቿ ላይ ተመስርታ ነው።

እውነተኛ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ማዕዘን ድንጋይ የሌሎችን ዱካ በዕውር ድንብር መከተል ሳይሆን የራስን ታሪክ፣ የሰላም ቀመሮች እና ማኅበራዊ ትስስሮች አብጠርጥሮ ማወቅና በሥራ ላይ ማዋል ነው።

የመደመር ፍልስፍና ማዕከላዊ ሐሳብ የሆነው "ወደ ውስጥ የመመልከት" መርህ ትልቁ የድል ምስጢራችን ነው።

ይህ ማለት የውጭ መፍትሔን ብቻ ከመጠባበቅ በመውጣት የራሳችንን አቅም፣ ፈጠራ እና ማኅበራዊ ሀብት አቀናጅቶ መጠቀም ማለት ነው።

ከልብ የመነጨ እርቅ፣ ሰፊ የይቅርታ መንፈስ እና የሰላም ፍቅር ውስብስብ መዋቅራዊ ችግሮቻችንን በራሳችን ብቃት እየፈታን ወደ ላቀ የዕድገት ከፍታ የምንሸጋገርባቸው የማይናወጡ ምሰሶዎች ናቸው።

ለዚህ ዘላቂ ጽናት እና የሰመረ አብሮነት ሕያው ማሳያዎች ከሆኑት ታላላቅ የባህል ሀብቶቻችን መካከል የኢሬቻ የእርቅ እና የምስጋና ሥርዓት፣ እንዲሁም የመስቀል በዓል የአንድነት እና የብርሃን ተምሳሌትነታቸው በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

እነዚህ በዓላት የሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴትነታቸውን ተሻግረው የሰው ልጅ የጋራ ሀብት መሆናቸውን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር የመሰከረላቸው ናቸው።

የመስቀል በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መዝገብ ላይ የሰፈረ ሲሆን፣ ኢሬቻም ዕውቅና በተቸረው የገዳ ሥርዓት ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው አንጸባራቂ እሴት ነው።

ከዚህ ባለፈ እነዚህ በዓላት በዘመናችን ለሚገጥሙን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች ትልቅ የመፍትሔ ምንጭ ናቸው።

ወጣቱ ትውልድ ከውጭ ከሚመጣ ጫና ይልቅ በእነዚህ ሥርዓቶች ውስጥ ያለውን የመተባበር፣ የመደጋገፍ እና ልዩነትን አቻችሎ የመኖር ጥበብ በመቅሰም ለሀገር ግንባታ ሊጠቀምባቸው ይገባል።

ኢሬቻ ለአምላክ ምስጋና ከማቅረብ ባለፈ ሕዝብ የሚቀራረብበት እና የሰላም ማሰሪያ የሚሆንበት ታላቅ መድረክ ነው።

ልክ እንደዚሁ የመስቀል በዓል የመደመር እና የኢትዮጵያውያን የአንድነት ማሳያ በመሆን ሉዓላዊነት እና ሰላምን በዘላቂነት የሚጠብቁ የኅብረተሰባችን ልዕልና መገለጫዎች ሆነው ዘልቀዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በቀጣይም የሚገጥሟትን ውስብስብ የውስጥም ሆነ የውጭ ፈተናዎች በድል ማለፍ የምትችለው፣ እነዚህኑ የሰመረ ማኅበራዊ እሴቶች እና ሀገር በቀል እውቀቶች በማስፋት ነው።

የጋራ ዕድገታችን፣ የሰላማችን እና የጸናች ሀገረ መንግሥት ግንባታችን ምስጢር የሚገኘው በባህላችን ጥልቀት ውስጥ ባሉ የብርሃን እና የሰላም ከፍታዎች ላይ በመሆኑ፣ ዘወትር መነሻችንም መድረሻችንም የራሳችንን አቅም አሟጦ መጠቀም ሊሆን ይገባል።

በሔዋን ጌታቸው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: