Search

የመቄዶንያ ማዕከል ግንባታን የሚያፋጥኑ ዘመናዊ ማሽነሪዎች እና የ'ፊኒሺንግ' ቁሳቁሶች ገቡ

ዓርብ መስከረም 15, 2019 83

የመቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማኅበር በኅብረተሰቡ ያልተቋረጠ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያስገነባ ለሚገኘው ማዕከል ግንባታ የሚውሉ ወሳኝ ግብዓቶችን ወደ ስፍራው ማጓጓዙን የማኅበሩ መሥራች አቶ ቢኒያም በለጠ አስታወቁ።

አቶ ቢኒያም እንደገለጹት ለማዕከሉ ግንባታ መጠናቀቂያ የሚውሉ የተለያዩ የማጠናቀቂያ (ፊኒሺንግ) ቁሳቁሶች፣ ዘመናዊ ማሽነሪዎች እና ሊፍቶች ወደ ማዕከሉ ገብተዋል።

በተለይም በዛሬው ዕለት የገቡት በአንድ ጊዜ እስከ 20 ሰዎችን የመጫን አቅም ያላቸው 7 ዘመናዊ ሊፍቶች፣ የማዕከሉን የውስጥ እንቅስቃሴ የሚያቀላጥፉ ናቸው።

ይህም ለአረጋውያን፣ ለሕመምተኞች እና በዊልቸር ለሚንቀሳቀሱ ዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት በተሻለ ደረጃ ለማድረስ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

ማኅበሩ ቀደም ሲልም በበጎ አድራጊዎች ድጋፍ 121 ባለ 40 ጫማ ኮንቴይነር የማጠናቀቂያ ዕቃዎችን እና ማሽነሪዎችን ማስገባቱ የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን የደረሱት ቁሳቁሶች የማዕከሉን የማስፋፊያ ሥራዎች በከፍተኛ ጥራት ለማጠናቀቅ ያስችላሉ ተብሏል።

ኅብረተሰቡ የሚያደርገው እገዛ በቀጥታ የዜጎችን ሕይወት ለመቀየር እና የማዕከሉን ዓላማ ለማሳካት እየዋለ መሆኑን የተናገሩት አቶ ቢኒያም፤ ለድጋፉ የተባበሩ የመንግሥት ተቋማትን፣ አጋር አካላትን እና መላውን ሕዝብ አመስግነዋል።

በሰናይት ሠይፉ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: