ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚገነባው በግለሰቦች ፍላጎት ሳይሆን በጽኑ እና ዘላቂ ተቋማት መሠረት ላይ ነው።
ተቋማት ከግለሰቦች እና ከፖለቲካዊ ዑደቶች ተሻጋሪ ሆነው ሲደራጁ፤ የሀገርን ቀጣይነት፣ የሕዝብን እምነትና የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያስችሉ መዋቅራዊ መሠረቶችን ያጸናሉ።
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል ኦላኒ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የተቋም ግንባታ የመደመር እሳቤ ዋና አካል መሆኑን ገልጸዋል።
የትናንት መልካም ልምዶችን መጠቀም፣ የተበላሹ አሠራሮችን ማስተካከልና ከሌሎች አዎንታዊ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ተቋማትን ማጠናከር የዚሁ እሳቤ መገለጫ እንደሆነም ተናግረዋል።
በተጨማሪም በግሉ ዘርፍ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን እምቅ አቅም አውጥቶ ወደ ልማት ማስገባት እንደሚገባ ያመላከቱት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው፤ ጠንካራ ተቋማት ከተገነቡ የግለሰቦች ለውጥም ሆነ የፖለቲካ ሂደቶች መቀያየር የሀገርን ጉዞ እንደማያስተጓጉሉት አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የአመራርና የአስተዳደር ኮሌጅ ምክትል ዲን መሐመድ ዓሊ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ተቋማት በግለሰቦች ወይም በተወሰኑ ቡድኖች ፍላጎት እንዳይመሩ አሠራሮችን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያዳበረው የሽምግልና፣ የመቻቻል እና የአብሮነት ባህል ዘመናዊ እና ዘላቂ ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችል ትልቅ ማኅበራዊ አቅም መሆኑንም አብራርተዋል።
ጽኑ ተቋማት ያሉት ሀገር ግለሰቦች እና ፓርቲዎች ቢለዋወጡም ዘመናትን ተሻግሮ መቀጠል እንደሚችል ያነሱት ዶ/ር መሐመድ፤ ጠንካራ ተቋማት የፍትሕ ሥርዓትን፣ መልካም አስተዳደርን እና በሕዝቦች መካከል ያለን መተማመን የሚያጸና መሠረት እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።
በተለይም ሙስናን ለመከላከል ተቋማዊ ገደቦች እና የተጠያቂነት ሥርዓቶች መኖራቸው ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
የሀገረ መንግሥት ጽናት በምኞት ሳይሆን በጠንካራ ተቋማት ግንባታ እንደሚወሰን ያስገነዘቡት ባለሙያው፤ ተቋማት ተልዕኳቸውን በሙያዊነት፣ በተጠያቂነትና በተቋማዊ ቀጣይነት ሲወጡ፣ የሀገርን ልማትና ብሔራዊ ጥቅም በዘላቂነት ማገልገል ይችላሉ ብለዋል።
ለዚህም የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን አፈጻጸም ማሻሻል፣ የጸጥታና ደህንነት ተቋማትን በሙያዊነት ማጠናከር እንዲሁም ተቋማትን ከግለሰቦች ፍላጎት በላይ ተሻጋሪ ማድረግ የሀገርን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ወሳኝ አቅጣጫ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: