ቀይ ባሕር የምሥራቁን እና የምዕራቡን ዓለም እንዲሁም አፍሪካ እና እስያን የሚያገናኝ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር እና የኃያላን ሀገራት የትኩረት ማዕከል ነው።
ኢትዮጵያ ከነበረችበት የኩስመና ታሪክ ወጥታ ወደ ላቀ ጂኦ-ስትራቴጂያዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ቁመና ለመሸጋገር ከሚያስችሏት ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ፍትሐዊ የቀይ ባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ አንዱ እና ዋናው መሆኑን በመገንዘብ የመደመር መንግሥት በትኩረት እየሠራበት ይገኛል።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እና የልማት ራዕይ ሰንቃ የምትጓዘው ኢትዮጵያ፣ ዘላቂ እና አስተማማኝ የባሕር በር እንዲሁም ወደብ ከሌላት የመኖር ሕልውናዋ አደጋ ውስጥ ይወድቃል።
ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያን "የመልክዓ ምድር እስረኛ" የሚያደርጋት ሲሆን፣ ብሔራዊ ጥቅሟም በሌሎች ሀገራት እንዲበየን በማድረግ የጥገኝነት አደጋ ደቅኖባታል።
በመሆኑም የባሕር በር ማግኘት ለሀገራችን ወጪ እና ገቢ ንግድ፣ ለኢንዱስትሪ ዕድገት እና ለብሔራዊ ደኅንነት ወሳኝነት ያለው የሕልውና ጉዳይ ነው።
በታሪክ አጋጣሚ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የባሕር በር መብትን ማጣት፣ የአሁኑን ትውልድ ውድ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል።
ይህን አንገብጋቢ ሀገራዊ ጥያቄ ለመመለስ የመደመር መንግሥት እየተከተለው ያለው ስልት፣ በሕጋዊ ማዕቀፍ የተመራ ነው።
በዚህም ሀገራችን ዘላቂ፣ አስተማማኝ እና በቂ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን በመርሕ፣ በውይይት እና በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ መሠረት ለማሳካት በጽኑ እየሠራች ትገኛለች።
በተጨማሪም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተፈጠሩ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ እና ስትራቴጂያዊ የኢኮኖሚ ግንኙነቶችን በመጠቀም የወደብ አማራጮችን የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ይሁን እንጂ ይህን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ እና ፍትሐዊ ጥያቄ ሆን ብለው ለማዛባት የሚሞክሩ አካላት የተለያዩ ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ ይስተዋላል።
የእነዚህ አካላት ዋና ዓላማ በሀገር ውስጥ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ጥርጣሬን መዝራት እንዲሁም በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕር ሰላጤ ሀገራት ዘንድ ሥጋትን መፍጠር ነው።
ነገር ግን ይህ የባሕር በር አጀንዳ የአሁኑን ብቻ ሳይሆን፣ መጪውን ትውልድ ጭምር ከድህነት እና ከጥገኝነት አላቅቆ በሀገራዊ ልዕልና ሥር ለማኖር የሚደረግ ፍትሐዊ ጥያቄ ነው።
በመሆኑም ኢትዮጵያን ከጂኦ-ስትራቴጂያዊ ጥገኝነት አላቅቆ ወደ ላቀ ቁመና ለማሸጋገር ዘላቂ፣ በቂ እና አስተማማኝ የባሕር በር ማግኘት ወሳኝ ነው።
ይህን የሀገራችንን ፍትሐዊ ጥያቄ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም ጎረቤት እና መላው የአፍሪካ ሀገራት በአግባቡ ተረድተው አጋር እንዲሆኑ የሚያስችል ያላሰለሰ የዲፕሎማሲ ሥራ ማከናወን ትልቅ ድርሻ አለው።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: