Search

"መስቀል የሕይወታችን መሠረት፣ የድኅነታችንም ዓርማ ነው"፡- መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል

ቅዳሜ መስከረም 16, 2019 131

የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከሚከበሩ ታላላቅ እና ድምቀት ካላቸው በዓላት አንዱ ነው።

በዓሉ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በንግሥት እሌኒ መገኘቱን በማሰብ መስከረም 17 ቀን የሚከበር ሲሆን፣ መስከረም 16 ቀን ደግሞ የቅድመ በዓሉ "ደመራ" ይከናወናል።

የመስቀል በዓል አከባበር ሥነ ሥርዓት ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲቀጥል፣ እ.ኤ.አ በ2013 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ተመዝግቧል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ የጥናት እና ምርምር መምሪያ እንዲሁም የቅዱስ ሲኖዶስ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ከኢቢሲ ዶት ስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በዓሉን የምናከብረው የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከተቀበረበት የወጣበት ዕለት በመሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ በዓል ነው ብለዋል።

የበዓሉ መሠረታዊ ትርጉም ከነገረ መስቀሉ እና ከነገረ ድኅነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ያነሱት መምህሩ፣ ቅዱስ ጳውሎስ በመልዕክቱ "ከክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ" ማለቱን በማስታወስ፣ መስቀል ለክርስቲያኖች የጥበቃ፣ የድኅነት ዓርማ፣ የትምክህት እና የክርስትና ማንነት መገለጫ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።

"መስቀል ድኅነት የተፈጸመበት፣ ከአምላካችን ጋር የታረቅንበት፣ እውነተኛው የሕይወት መሥዋዕት የተሠዋበት እና ገነት የተከፈተበት በመሆኑ የሃይማኖታችንን ትርጉም የምንሰብክበት ልዩ መገለጫችን ነው" ሲሉም አክለዋል።

"ስለ መስቀሉ ስንናገር ሁልጊዜ ስለ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እሱ ስለ ፈጸመልን ድኅነት እና ወደ እርሱ ስላቀረበን ልዩ ምሥጢር የምንናገር በመሆኑ ለኦርቶዶክሳውያን ልዩ ትርጓሜ አለው" ብለዋል።

"መስቀሉ አበራ" በማለት በዓለም ላይ ሁሉ ለሰው ልጆች ሕይወት በተገኘው የድኅነት ብርሃን የምንሰብክበት ነው ያሉት መምህር ዳንኤል፤ በዘንድሮው የመስቀል በዓል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር እምነት እና ሥነ ሥርዓት አንድ የሆኑት የሕንድ ማላንካራ ሲሪያን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በዓሉን እንደሚታደሙ ገልጸዋል።

ከሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመጡ የመዘምራን እንግዶችም እንደሚኖሩ አያይዘው ገልጸዋል።

አንድነታችንን፣ ሰላማችንን እና ፍቅራችንን በመጠበቅ፣ ለሀገር ዕድገት እና ለትውልዱ ደኅንነት በጋራ በመሥራት በዓሉን እንድናከብርም ጥሪ አቅርበዋል።

 

በሜሮን ንብረት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: