ከመስከረም እስከ መስከረም በሚፈራረቀው የጊዜ ሂደት ውስጥ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ሳይለቅ ዘመናትን የተሻገረው የኢትዮጵያውያን የመስቀል በዓል፣ በታላቅ ድምቀት የሚከበር መንፈሳዊ ሁነት ነው።
ይህም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በንግሥት እሌኒ አማካኝነት መገኘቱን ለማስታወስ የሚከናወን ነው።
በየዓመቱ ከመስከረም 16 የደመራ በዓል ጀምሮ እስከ መስከረም 17 የመስቀል በዓል ዕለት ድረስ በቤተክርስቲያኗ ሥርዓት መሰረት ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ ይከበራል።
የካህናቱ ያሸበረቀ አልባሳት፣ ያሬዳዊ ወረብ፣ የመዝሙራት ድምቀት እና የደመራው ችቦ የበዓሉን መንፈሳዊና ባህላዊ ግርማ ሞገስ አጉልተው ያሳያሉ።
በዩኔስኮ በማይዳሰስ የዓለም የባህል ቅርስነት የተመዘገበው ይህ በዓል የሚከበርበት የመስቀል አደባባይ፣ የሀገራችንን ታሪካዊና ማህበራዊ ሁነቶች በማስተናገድ ረገድ ትልቅ ቦታ ያለው ሥፍራ ነው።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት እና የመስቀል አደባባይ ዘመናዊ እድሳት ይህንን ታሪካዊ ስፍራ ሙሉ በሙሉ ወደ ተዋበና ምቹ የቱሪዝም ማዕከልነት ቀይሮታል።
አደባባዩ በስፋቱ በርካታ ታዳሚዎችን በአንድ ላይ ማስተናገድ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ፣ በአደባባዩ እና በአካባቢው በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት የተገነቡ አዳዲስ የስፖርትና የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ዘመናዊ የህዝብ መናፈሻዎች፣ የተዋቡ የመብራትና የውኃ ትርዒቶች፣ ሰፊ የእግረኛ መንገዶች እንዲሁም የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ይገኛሉ።
ይህም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች በነፃነት ለመንቀሳቀስ፣ ሁነቶችን ለመከታተልና የከተማዋን አዲስ ውበት ለመጎብኘት እጅግ ምቹና ማራኪ ከባቢን ፈጥሯል።
የመስቀል በዓል በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች እና ክልል ከተሞች በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። ይህ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቅ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሁነት ከኮሪደር ልማቱ አዲስ ገጽታ ጋር ተጣጥሞ ለሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ አቅም አጎልብቷል።
በመሆኑም ጎብኚዎች የኢትዮጵያን ጥንታዊ ባህል፣ የህዝቦቿን እንግዳ ተቀባይነት እና የዘመናዊቷን አዲስ አበባ እድገት በአንድ ላይ የሚያዩበት ልዩ አጋጣሚ ፈጥሯል።
በልዩ እሸቱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: