የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቱ ባሻገር፣ የኢትዮጵያውያንን የህብረት ውበት እና የጋራ ማንነት ድምቅ አድርጎ የሚያሳይ የታሪክ እና የባህል ኩራት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመስቀል በዓል ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፣ የደመራን ሂደት ከመደመር ፍልስፍና ጋር በማያያዝ ያቀረቡት ሐሳብ የበዓሉን ሕብረተሰባዊ እና ሀገራዊ ትርጉም በላቀ ደረጃ አጉልቶታል።
በመልዕክቱ እንደተገለጸው፣ ደመራ በባህሪው የአንድነትና የጋራ ጥረት ውጤት ነው። አንድ ነጠላ እንጨት ብቻውን ደመራ ሊሆን እንደማይችል ሁሉ፣ ብቸኛ እንጨት ለብቻው የሚያፈነጥቀው ብርሃንም ሆነ የሚሰጠው ሙቀት የተወሰነ ነው።
ነገር ግን በርካታ የተለያየ መጠን እና ቅርጽ ያላቸው እንጨቶች ተሰብስበው፣ ተደራጅተው እና ተደምረው ሲቆሙ ግዙፉንና አብሪውን ደመራ ይፈጥራሉ። ይህ ሂደት የመደመርን ኃይልና አስፈላጊነት በግልጽ የሚያሳይ ህያው ተምሳሌት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳመላከቱት፣ በደመራ ውስጥ ረጅም፣ አጭር፣ ወፍራም እና ቀጭን እንጨቶች እንደየባህሪያቸው ቦታ ይይዛሉ። ሀገርም እንዲሁ የሁሉም ዜጎች ልዩ ልዩ እውቀት፣ አቅምና ባህል ተደምሮ የሚገነባ የጋራ ቤት መሆኗን ያሳያል።
ነጠላ እንጨቶች ተበታትነው ሲቀመጡ የሚኖራቸው ፋይዳ አነስተኛ ነው። ተሰብስበው ሲደመሩ ግን አካባቢውን የሚያበራ፣ ሙቀት የሚሰጥና የደስታ ምልክት የሚሆን ታላቅ እሳት ይፈጥራሉ።
የኢትዮጵያውያንም ሕብረትና መደመር ሀገራዊ ፈተናዎችን አሸንፎ ወደ ታላቅ ብርሃንና ብልጽግና የሚያሸጋግር ኃይል ነው። ደመራ ለመሥራት ሕብረተሰቡ በአንድነት ይተማመናል፣ እንጨት ይሰበስባል፣ አብሮ ይተክላል። ይህ የጋራ ሥራና ውህደት ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት የሚያስፈልገውን ጠንካራ የትብብር መንፈስ የሚያንጸባርቅ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት የመስቀል እና የደመራን በዓል ከባህላዊ ሁነቱ ባሻገር፣ ለሀገር ግንባታ እና ለሕዝቦች አንድነት ትልቅ ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን ያመላክታል።
ከነጠላ እንጨት ስብስብ እስከሚበራው ደመራ ያለው ሂደት፣ ኢትዮጵያውያን በመደመር፣ በትብብርና በአንድነት ከቆሙ የትኛውንም ፈተና አልፈው ሀገራዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚችሉ የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው።
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: