Search

ከክረምቱ ጨለማ በኋላ የሚፈካው የተስፋ ብርሃን፦ የዘመን መሻገሪያዋ ውብ አደይ አበባ

ቅዳሜ መስከረም 16, 2019 130

ጭጋጋማው ክረምት አልፎ፣ ደመና አዝሎ የቆየው ሰማይ በጠራራ ፀሐይ ሲተካ ተፈጥሮ አዲስ ምዕራፍ መጀመሯን በራሷ ቋንቋ ታበስራለች።

መስኩ አረንጓዴ ምንጣፉን ሲዘረጋ፣ ያንን ውብ የተፈጥሮ ጥሪ የተከተሉ ሁሉ የአዲስ ዓመት ብስራትን በመናፈቅ ወደ መስኩ ያተኩራሉ።

በዚህ ሁሉ የተፈጥሮ ውበት መሃል ደግሞ ቢጫ ውበታቸውን አጉልተው ፈክተው ብቅ የሚሉት አደይ አበባዎች፣ የአዲስ ዘመንን ብሩህ ተስፋ ይዘው ይከሰታሉ።

የዘመን ለውጥ አብሳሪዋ የመጀመሪያዋ አደይ አበባ ስትፈካ፣ እያንዳንዱ ሰው የራሱን የዘመን ትዝታ ለማውሳት እና አዲስ ተስፋን ለመሰነቅ ልቡ ወደ መስኩ ይሸፍታል።

ወቅቱን ጠብቆ በሚለመልመው መስክ ላይ የሚታየው የዚህች ውብ አበባ ፍካት፣ በሰው ልጅ መንፈስ ውስጥ የተስፋ ብርሃን እና አዲስ ብርታት የመስጠት ድንቅ ተፈጥሯዊ ኃይል አለው።

ለመሆኑ መስከረም ሲጠባ በተለይም በተራራማው የሀገራችን ክፍል በብዛት የምታበበው ይህች ድንቅ አበባ ከጀርባዋ ምን ዓይነት ምስጢር ይዛ ይሆን?

በሳይንሳዊ አጠራሯ “ባይደንስ ማክሮፕቴራ” (Bidens macroptera) በመባል የምትታወቀውና “እናት አበባ” እየተባለች የምትጠራው አደይ አበባ፣ ልዩ የፍጥረት ውበት ናት።

በአፍሪካ አህጉር ከሚገኙ 64 ያህል የአደይ አበባ ዝርያዎች መካከል ወደ 20 የሚሆኑት በኢትዮጵያችን አፈር ላይ የሚበቅሉ ሀገር በቀል ሃብቶቻችን ናቸው።

ይህች ድንቅ እፅዋት ዘሯ ለዘጠኝ ረጅም ወራት ያህል መሬት ውስጥ ተሸሽጎ ከቆየ በኋላ፣ በሰኔ እና በሐምሌ ወር የዝናብ ወራት መብቀል ትጀምራለች።

በመቀጠልም ከመስከረም እስከ ኅዳር ባሉት ሦስት የወርቃማ ወራት ጊዜያት መስኩን በቢጫ ህብረ-ቀለሟ አጊጣ፣ ለዐይን ማራኪ በሆነ ውበቷና በጥሩ መዓዛዋ አካባቢውን ታደምቃለች።

የውጭ ሀገር ዜጎች “Ethiopian Meskel Daisy” እያሉ የሚጠሯት ይህች ሀገር በቀል እፅዋት፣ የተፈጥሮ ታላቅ ገጸ-በረከት እና የዘመን መሻገሪያ ምልክታችን ናት።

ከውበቷና ከተስፋ ምልክትነቷ ባሻገር፣ አደይ አበባ በሳይንሳዊም ሆነ በሀገር በቀል እውቀት የተረጋገጠ መድኃኒትነቷም ይነገራል።

በተለይም የሀገር ባህል መድኃኒት ቀማሚዎች የአበባዋን ቢጫ ክፍል ወስደው በማድረቅ እና ወደ ዱቄትነት በመቀየር ከማር ጋር በመለወስ ለፊት ቆዳ እንክብካቤና ውበት ይጠቀሙበታል።

የክረምቱን ጨለማ ገልጣ በብርሃን የተካችው አደይ አበባ፣ ዛሬም ለእያንዳንዳችን አዲስ ተስፋን እና አዲስ ስኬትን እያበሰረች ፍካቷን ቀጥላለች።

 

በመሐመድ ፊጣሞ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: