Search

ቀጠሮ የማያዛንፉት የመስቀል ስጦታዎች

እሑድ መስከረም 17, 2019 60

የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከአሮጌ ወደ አዲስ መሸጋገሪያ ስለመሆኑ እንኳን ሰው ተፈጥሮም ደምቃ ነው የምትታየው።

ታዲያ ከዚህ የአዲስ ዘመን ብስራት ውስጥ ሁሌም የማይቀሩት ምስጢረኞቹ የመስቀል ወፍ እና የአደይ አበባ ቀጠሯቸውን ሳያዛንፉ በመስከረም ብቅ ሲሉ ከአስገራሚው ውበታቸው ጋር ነው።

የመስቀል ወፍ እና አደይ አበባ ከመስከረም በፊትም ሆነ ከመስከረም በኋላ አይታዩም። በእርግጥ የመስቀል ወፍ የምንላት ሁሌም አብራን የምትኖር ብትሆንም ቀለሟ የሚቀየረው ግን በመስከረም ብቻ ነው።

የመስቀሏ ወፍ ላባዋን እንደምትቀይረው ኢትዮጵያውያንም ራሳቸውን አንጽተው ለቀጣዩ ፍሬያማ ጉዞ ይዘጋጃሉ። ምድር በአደይ አበባ እንደምታጌጠው ኢትዮጵያውያንም በፀዓዳ ልብሳቸው ያጌጣሉ።

መስከረም እና መስቀልን ኢትዮጵያውያን ደመራ ደምረው ሕብራቸውን ያደምቁበታል፤ ችቦ አብርተው መጻኢ ብርሃናቸውን ያዩበታል። ይህ ተፈጥሮን የተከተለ አከባበር በውስጡ በርካታ ምሥጢሮችን የያዘ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሀብትም ነው።

መስቀል ሲመጣ ደግሞ ቀጠሮአቸውን የማያዛንፉት የመስቀል ወፍ እና አደይ አበባ የኢትዮጵያ ተስፋ ብስራት አድማቂዎች ናቸው። ባለቅኔው መንግሥቱ ለማ፦

"የመስቀል ወፍ እና አደይ አበባ፣

ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ፤

ማን ያውቃል…?"

በማለት የሁለቱ የማይዘነፍ ቀጠሮ ምሥጢር እንደሆነ ተቀኝተዋል።

እነዚህ ፍጥረታት በመስከረም ብቻ ደምቀው የሚከሰቱት ባለቀጠሮዎች የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ምሥጢሮች ብንላቸው የሚገባቸው ነው።

ሁለቱም ፍጥረታት ቀድመው በነሐሴ አይመጡም፤ ቆይተው ጥቅምት ውስጥ አይታዩም። እኛ በመስከረም እናያቸዋለን እንጂ ሁሌም አብረውን መኖራቸው ደግሞ ሌላው ምሥጢራቸው ነው።

አደይ አበባም ቀድሞ በነሐሴ አይከሰትም፤ ዘግይቶም በጥቅምት አይታይም። ለዚህም ነው አብዬ መንግሥቱ የወፏን መምጫ ጊዜ እና የአደይ አበባን አብሮ መከሰት እንደ ተፈጥሮ ምሥጢር አድርገው የሚያጠይቁት።

አደይ አበባ ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ እየደረቀ ሲሄድ ምንም ፍሬ ያለው አይመስልም፤ ከዚያ በኋላ ቅጠሉ እንኳን በምድር ላይ አይታይም። በጋውን ሙሉ እየዘነበ ከርሞ በሚያዝያ ወይም ግንቦት ብራ ቢሆን ወይም ከዚያም አልፎ ሐምሌ እና ነሐሴ ላይ ብራ ቢሆን አደይ አበባ ያለ ጊዜው አይታይም።

የመስቀል ወፍም እንዲሁ ከመስከረም ውጭ ያሉ ወራት ላይ ከመስከረም ጋር ተመሳስለው ቢመጡ እንደ መስቀል ጊዜ አትከሰትም (የላባዋን ቀለም አትቀይርም)።

መስከረም ያለው ስሜት የትኛውም ወር አይኖረውም። በዚህ ወር የሚታዩ የተፈጥሮ ክስተቶች በጣም ልዩ ናቸው። አደይ አበባ ጋራ ሸንተረሩን በቢጫ ልብሱ ሲያጌጥ፣ የመስቀል ወፍ ደግሞ ጎጆዋን ሠርታ ሽር ጉድ ስትል ልዩ ሕብር ይፈጥራሉ። የእነዚህ ብርቅዬዎች መከሰት ከጠራው ሰማይ ጋር ሲዋሃዱ ደግሞ ነፍስን በሐሴት ይሞላሉ።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: