Search

የዘንድሮው የዓለም ቱሪዝም ቀን እና የኢትዮጵያ ቀድሞ የመዘጋጀት ብቃት

እሑድ መስከረም 17, 2019 58

ኢትዮጵያ የተፈጥሮን መታደስ ከሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ እሴቶች ጋር አዋህዶ የያዘውን የመስቀል በዓል እያከበረች ባለችበት በዚህ ቀን ዓለማችንም የቱሪዝም ቀንን እያከበረች ነው።

የዘንድሮው የዓለም የቱሪዝም ቀን "ዲጅታል አጀንዳ እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ለቱሪዝም አዲስ ቅኝት" በሚል እጅግ ወቅታዊ መሪ ቃል ነው የሚከበረው።

ሀገራችንም የዘንድሮውን የመስቀል ደመራ በዓልን ያከበረችው ላለፉት 18 ዓመታት ሳይሻሻል ከቆየ በኋላ ጸድቆ ወደ ሥራ የገባው አዲሱ የቱሪዝም ፖሊሲ ጋር ነው።

ይህ ፖሊሲ ለዲጂታል አሠራሮች፣ ለቴክኖሎጂ ፈጠራዎች እና በተለይም ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑ ደግሞ ከዓለም ቱሪዝም ቀን መሪ ቃል ጋር በእጅጉ የተጣጣመ እና ቀድሞ የመዘጋጀት ብቃታንን ያሳየ ሆኗል።

የዲጂታል ለውጥ እና የኤ.አይ መተግበሪያዎች በቱሪዝም ልማት ውስጥ ያላቸውን እያደገ የመጣ ሚና ከግምት ውስጥ ያስገባው ይህ ፖሊሲ፣ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ተወዳዳሪነት እና ዘላቂ ዕድገትን ለማጠናከር ትልቅ አቅም ነው።

የዓለም ቱሪዝም ድርጅት እንዳስገነዘበው፣ ዛሬ ላይ ቱሪስቶች የት መሄድ፣ ምን ማየት እና የት ማረፍ እንዳለባቸው የሚመራቸው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ነው። ቴክኖሎጂው የቱሪዝሙን ዘርፍ ከሥሩ እየቀየረው ባለበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ አዲሱ የቱሪዝም ፖሊሲም ይህንን ዓለም አቀፋዊ የቴክኖሎጂ ሽግግር በአግባቡ ለመምራት ያስችላል።

የቱሪስቶች መስህብ የሆኑት በሀገራችን ያሉ ነባር እና በገበታ ፕሮጀክቶች የተገነቡ አዳዲስ መዳረሻዎቻችን በዚህ የዲጂታል ዓለም ውስጥ የራሳቸው ጠንካራ ድምፅ ይኖራቸዋል።

የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓትነቱ ባሻገር የሀገራችን የቱሪዝም የጀርባ አጥንት ነው። በመስቀል አደባባይም ሆነ በመላው ሀገራችን ደመራው ሲለኮስ የሚፈጠረው የብርሃን ጸዳል እና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ቀልብ የሚስብ ኃይለኛ ማግኔት ነው።

ዛሬ ላይ የደመራው ብርሃን በመስቀል አደባባይ እና በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በመላው ዓለም በሚገኙ የዲጂታል መስኮቶች ጭምር ደምቆ ታይቷል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ለዓለም አቀፍ ተጓዦች መረጃ ሲሰጥ፣ የኢትዮጵያን ባህል እና የመስቀልን ደማቅ በዓል ቀዳሚ ምርጫው አድርጎ እንዲያቀርብ የዲጂታል ዐሻራችንን ማሳደግ በእጅጉ አስፈላጊ ነው።

ደማቁን የመስቀል ደመራ ኩነት በከፍተኛ ጥራት በተነሡ ምስሎች፣ እንዲሁም በሰው ሠራሽ አስተውሎት በታገዙ ማራኪ የመረጃ አቀራረቦች በማዘጋጀት ለዓለም ማድረስ ወሳኝ ነው።

ኢቢሲ ዶትስትሪም ይህንን ጥንታዊ ታሪክ ዘመናዊው ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኢትዮጵያን ውበት በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ተመልካቾች አድርሷል። ይህም ሀገራችን ዕንቁ ባህሏን በዘመናዊው የቴክኖሎጂ ዓለም ውስጥ አጉልታ ለማሳየት እና ተጠቃሚ ለመሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኗን አንዱ ምስክር ነው።

በዮናስ በድሉ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: