Search

“ሕይወት በአብያተ መንግሥታት” የተሰኘ ልዩ መርሐ ግብር በፋሲል አብያተ መንግሥት ግቢ ተካሄደ

እሑድ መስከረም 17, 2019 39

የዓለም ቱሪዝም ቀን አከባበርን በማስመልከት “ሕይወት በአብያተ መንግሥታት” የተሰኘ ልዩ መርሐ ግብር በታሪካዊው የፋሲል አብያተ መንግሥት ግቢ ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሣ፣ የኢትዮጵያን የበዓላት ዕሴት፣ የታሪካዊ እና የባህላዊ ቅርሶች ትርጉም ሳይዛባ ተጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በድምቀት የሚከበሩ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓላት ለቱሪዝም ዘርፉ ዕድገት ተጨማሪ ትልቅ ዕድል መሆናቸውንም አክለው አስረድተዋል።

እነዚህን ሀገራዊ እና መንፈሳዊ በዓላት ለመታደም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከሚመጡ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች የሚገኘው ገቢም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች በአግባቡ በመጠበቅ እና በስፋት በማስተዋወቅ ዘርፉን በዓለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ተወዳዳሪ ለማድረግ፣ በተለይም በዲጂታል አማራጮች ላይ ሰፊ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በ"ሕይወት በአብያተ መንግሥታት” መርሐ ግብር ላይ የፋሲል ቤተ መንግሥት ጉብኝት የተካሄደ ሲሆን፣ የቀደመውን የቤተ መንግሥቱን ሕይወት፣ የአኗኗር ሥርዓት እና ታሪካዊ ክንውኖች ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ማራኪ ትዕይንቶች ለታዳሚዎች ቀርበውበታል።

በማሕሌት ታደለ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: