የቦሮ ሽናሻ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ "ጋሪ-ዎሮ" በዓል "ጋሪ-ዎሮ ለአብሮነት እና ለባሕል ልማት" በሚል መሪ ቃል በአሶሳ ከተማ በድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የጋሪ-ዎሮ በዓል ለትውልድ እንዲተላለፍ ትኩረት ተደርጎበት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን ባሕል እና ዕሴቶች ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ የሕዝቡን የባሕል ማዕከላት ግንባታ በትብብር እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በዓሉ በብሔረሰቡ ዘንድ የዘመን መሻገሪያ በዓል በመሆኑ ይቅርታን፣ መረዳዳትን እና ምስጋናን ለፈጣሪ በማቅረብ የሚከበር መሆኑንም አቶ አሻድሊ ጠቅሰዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሪት ሚስኪያ አብደላ በበኩላቸው፣ ክልሉ የብዙኃን ባህል ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል።
በሽናሻ ብሔረሰብ ዘንድ የሚከበረው የ"ጋሪ-ዎሮ" በዓል ያለፈውን በይቅርታ በማሳለፍ፣ ማኅበረሰቡን በማስተሳሰር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፤ ይህ በዓል ለትውልድ እንዲሸጋገር በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በዓሉ ፍቅር እና ይቅርታን በማጠናከር ማኅበራዊ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን የቦሮ-ሽናሻ ልማት ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገብረ ሚካኤል ጉድሬ ገልጸዋል።
የ"ጋሪ-ዎሮ" በዓል ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲጠነክር የጎላ ፋይዳ ያለው ሲሆን፣ ትውፊቱን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ትኩረት ይደረግበታል ተብሏል።
በነስረዲን ሀሚድ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: