'ታላቅ ርዕይ፣ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ' የሚለው አስተሳሰብ የኢትዮጵያን ታሪካዊ መሠረት፣ ስትራቴጂያዊ የጂኦ-ፖለቲካዊ ስፍራ እና የሕዝብ ቁጥር ገዢነት ማዕከል ያደረገ ጥልቅ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ፍልስፍና ነው።
ይህ እሳቤ ኢትዮጵያ ካጋጠሟት መዋቅራዊ እና አህጉራዊ ፈተናዎች በመውጣት፣ ኢኮኖሚዋን በገበያ መሪነት ለማዘመን፣ ዲፕሎማሲዋን ለማስፋፋት እና የደኅንነት አቅሟን በራስ አቅም ለመገንባት የምታደርገውን ጠንካራ ጉዞ ያሳያል።
ላለፉት ዓመታት በመደመር መንግሥት የተወሰዱት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ የተመዘገቡ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች እና የተቋማት መዘመን ይህን እሳቤ ከተጠበቀው በላይ ወደ ተጨባጭ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ አቅም ቀይረውታል።
የማክሮ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለዚህ ስኬት ዋነኛ ሞተር ነው። በሐምሌ 2016 ዓ.ም የጀመረው ሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ኢትዮጵያን ለዓመታት ሲፈታተን ከነበረው የውጭ ምንዛሬ ገበያ መዛባት እና የፋይናንስ ቀውስ ያወጣ ስትራቴጂያዊ እርምጃ ነው።
ቀደም ሲል የነበረው መዋቅር የግል ዘርፉን በማራቅ እና የመንግሥትን የዕዳ ሸክም በማብዛት የምርታማነት ማነቆ ሆኖ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ፣ የወለድ ተመንን መሠረት ያደረገ የገንዘብ ፖሊሲ መተግበሩ እና ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የበጀት ጉድለት በቀጥታ የሚያደርገውን ብድር ማስቀረቱ ፈጣን የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን አምጥቷል።
የውጭ ምንዛሬ ገበያው በገበያ መሪነት እንዲተመን መደረጉን ተከትሎ በትይዩ ገበያ እና በባንክ መካከል የነበረው ሰፊ የምንዛሬ ልዩነት በከፍተኛ ፍጥነት ጠብቦ ገበያውን ጤናማ አድርጓል።
ይህ እርምጃ የወጪ ንግድ ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ በማነቃቃት የውጭ ንግድ ገቢያችንን አሳድጎታል። በማዕድን እና በቡና የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው።
ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ በመተግበሩ ከ30 በመቶ በላይ የነበረው የዋጋ ንረት በተከታታይ ወራት እያሽቆለቆለ መምጣቱን የፖሊሲ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የመንግሥት የበጀት ጉድለት ከጠቅላላ ምርት አንፃር ከ1.8 በመቶ በታች እንዲወርድ መደረጉ እና የታክስ አስተዳደር በዲጂታል ሥርዓት መደገፉ የኢትዮጵያን የፊስካል ጥንካሬ በሚገባ አረጋግጧል።
በተያዘው በጀት ዓመት የኢኮኖሚ ዕድገቱ 10.2 በመቶ ይደርሳል ተብሎ መገመቱ የዚሁ ፖሊሲ ስኬት ማሳያ ነው።
የኢኮኖሚ ዕድገት መዋቅራዊ መሠረት ከፍጆታ እና ከመንግሥት ወጪ መሪነት ወደ አምራች ዘርፎች ማለትም ወደ ማዕድን፣ አግሮ-ኢንዱስትሪ እና ማኑፋክቸሪንግ ተሸጋግሯል።
በማዕድን፣ በማኑፋክቸሪንግ እንዲሁም በግብርና ዘርፎች የተመዘገበው ፈጣን ዕድገት ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻል እና ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት ያፋጠኑ እርምጃዎች ናቸው።
ይህን የኢኮኖሚ አቅም ይበልጥ ዘላቂ የሚያደርጉት ታላላቅ የኃይል፣ የሎጂስቲክስ እና የኤቪዬሽን መሠረተ-ልማቶች ናቸው።
በተለይም ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ታላቅነቷን ያስመሰከረችበት ነው።
ይህ ግዙፍ የትውልድ ዐሻራ የውስጥ የኢንዱስትሪ ኃይል ፍላጎትን ከመሸፈን አልፎ፣ ለጎረቤት ሀገራት አስተማማኝ የመብራት ምንጭ በመሆን ቀጣናውን በኢኮኖሚ እያስተሳሰረ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል በተደረገ አጋርነት በጅቡቲ እና በደዋሌ መካከል የሚገነባው የ120 ኪሎሜትር የነዳጅ ቧንቧ መስመር የሎጂስቲክስ ማነቆዎችን በመቅረፍ የኃይል ደኅንነትን አስተማማኝ ያደርጋል።
ሌላው የኢትዮጵያን የታላቅነት ከፍታ የሚያሳየው የጉባ ብሥራት የሆነው እና በቢሾፍቱ ከተማ የሚገነባው ግዙፉ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ነው።
ይህ በአፍሪካ ትልቁ የኤቪዬሽን ማዕከል ለመሆን ታልሞ በከፍተኛ ትጋት እየተገነባ ያለው ፕሮጀክት ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ንግድ፣ ቱሪዝም እና ትራንዚት ዋነኛ መዳረሻ ያደርጋታል።
የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ ሰላማዊ የኑክሌር ኃይል ፕሮጀክት እና በ5 ዓመታት የሚገነቡት 1.5 ሚሊዮን ቤቶች የኢትዮጵያን ከፍታ እና የማድረግ አቅም የሚያንጸባርቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ናቸው።
በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎችም የንግድ ማዕከላትን ጥራት ከመጨመራቸውም በላይ የግል ኢንቨስትመንትን እና የቱሪዝም ዘርፍን በመሳብ ብሔራዊ ምርታማነትን እያሳደጉ ይገኛሉ።
እነዚህ ተጨባጭ የማክሮ ኢኮኖሚ ስኬቶች እና የግዙፍ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ወደ ላቀ አምራች ኃይል በመቀየር ታላቅ ርዕይዋን እውን እያደረገች መሆኗን በተግባር የሚያረጋግጡ ናቸው።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: