Search

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ከመደመር ዕሳቤ ጋር ማጣመር ለሀገራዊ ችግሮች ሀገር በቀል መፍትሔዎችን ለማመንጨት ዕድል ይፈጥራል - ሰለሞን ሙሉጌታ

እሑድ መስከረም 17, 2019 131

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የቴክኖሎጂ ዕድገት ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ የሚያስብበትን፣ ችግሮችን የሚፈታበትን እና መፃኢ ጊዜን የሚቀርጽበትን መንገድ እየቀየረ ያለ የቴክኖሎጂ ሽግግር ነው ሲሉ የቴክኖሎጂ ባለሙያው ሰለሞን ሙሉጌታ ገለጹ።

ባለሙያው ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የቴክኖሎጂ ዕድገቱ በፍጥነት እየተስፋፋ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያም በዚህ ሽግግር ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ መሆን እንዳለባት ሰለሞን ሙሉጌታ አስገንዝበዋል።

በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚመራውን የቴክኖሎጂ ሽግግር በባለቤትነት መምራት አለመቻል በዕድገት ምኅዳሩ ውስጥ ወደኋላ የመቅረት አደጋን ያስከትላል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም (ዶ/ር) አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ልጅ የሚያስብበትን፣ የሚሠራበትን እና ዕድሎችን የሚመለከትበትን መንገድ እየቀረጸ መምጣቱን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ በዚህ የቴክኖሎጂ ሽግግር ውስጥ ራሷን ማሳተፍ እንዳለባት አመልክተዋል።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂን ከመደመር ዕሳቤ ጋር ማጣመርም ለሀገራዊ ችግሮች ሀገር በቀል እና ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማመንጨት ዕድል እንደሚፈጥር ነው የገለጹት።

በተለይም የወጣቶችን የፈጠራ አቅም ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር በማጣመር በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርት እና በፋይናንስ ዘርፎች የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የAI አቅም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የAI ኢንስቲትዩት መቋቋሙ እና የAI ዩኒቨርሲቲ ለመጀመር የተያዘው ዕቅድ ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ከሚያሳዩ እርምጃዎች መካከል መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሰለሞን ሙሉጌታ በ2030 የAI ዘርፍ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ 15.7 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር አስተዋፅዖ ሊያደርግ እንደሚችል የተጠቀሰውን ግምት አንሥተዋል።

አፍሪካ ከዚህ ኢኮኖሚያዊ ዕድል 10 በመቶ ድርሻ ማግኘት ብትችል ከ1.5 ትሪሊየን ዶላር በላይ የሚደርስ ኢኮኖሚያዊ አቅም ሊፈጠር እንደሚችል፣ ኢትዮጵያም ከዚህ ዕድል የራሷን ድርሻ ለማግኘት የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ አቅሟን ማሳደግ እንደሚገባት ጠቁመዋል።

AI እንደ ዲጂታል መዝናኛ ወይም የቴክኖሎጂ ማሳያ ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ከኢኮኖሚ ዕድገት እና ከምርታማነት ጋር የተያያዘ መሣሪያ መሆኑንም ገልጸዋል። በግብርና የአየር ንብረት እና የምርት መጠን ትንበያን፣ በጤና ዘርፍ ፈጣን የሕክምና ምርመራን፣ በፋይናንስ ደግሞ አካታች የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማስፋፋት AI ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይችላል።

በዚህ መሠረት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ቅንጦት ሳይሆን የዲጂታል ሽግግር፣ የፈጠራ አቅም ልማት እና የኢኮኖሚ ዕድገት አዲስ አቅም እንደሆነ ተጠቁሟል።

በኢንቲሃድ አብራር

 

 

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: