ኢትዮጵያ በስፋቷ፣ በገዘፈ ታሪኳ፣ በእምቅ ሀብቷ እና በአሻጋሪ ልጆቿ አቅም ልክ ራሷን ጠብቃ ትውልድ መሻገር የምትችል፤ ታላቅ ራዕይ እና ትልቅ ሕዝብ ያላት ታላቅ ሀገር ናት።
ይህች ሀገር የሚገባትም ልክ እንደ ስሟ እና ግዝፈቷ ትልቅ ሥፍራ ሲሆን፣ የዚህ አዲስ ታሪክ ሠሪዎች የመሆን ወርቃማ ዕድል ደግሞ በእኛ በመደመር ትውልድ እጅ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያን አዲስ ታሪክ የመጻፍ ይህ የለውጥ ጉዟችን ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ደግሞ ከነገው ብሩህ ተስፋችን ጋር የምናስተሣሥርበት ትልቅ የታሪክ መስታወት ነው።
ትናንት ያልተጠናከረ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት፣ የዴሞክራሲ እጦት እና ከአካባቢያዊነት ትርክቶች ጋር የተያያዙ ፖለቲካዊ ግጭቶች ክፉኛ ሲፈትኗት የነበረችው ሀገራችን፣ ዛሬ በሀገራዊ ምክክር፣ በአፋኝ ሕጎች ማሻሻያ እና በሀገር በቀል ሪፎርሞች ታግዛ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጠነከረበትን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ከፍታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህን ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ እና የትውልድ አደራ ሲገልጹ "ትልቅ ሀገር የሆነችውን ኢትዮጵያ በስፋቷ፣ በታሪኳ እና በሀብቷ ልክ ለልጆቿ መሸጋገር መቻሏን ማረጋገጥ ያስፈልጋል" ብለዋል።
ቀደም ሲል የብክነት እና የመዘግየት ምልክት የነበሩ የመንግሥት ፕሮጀክቶች፣ ዛሬ በአዲስ የሥራ ባህል እና በጥብቅ ክትትል የዘመናት ብልሽታቸውን አራግፈዋል። ፕሮጀክትን አቅዶ መጀመር ብቻ ሳይሆን በተያዘለት ጊዜ እና ጥራት በፍጥነት ማጠናቀቅ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ መለያ ሆኗል።
በከተሞቻችን በስፋት የምናየው የኮሪደር ልማት፣ የቱሪዝም አቅምን ያጎለበቱት የገበታ ፕሮጀክቶች ዐሻራዎች እና የዲጂታል ኢትዮጵያ መሠረተ ልማቶች የዚህ አዲስ የሥራ ዲሲፕሊን ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው።
በሁሉም የልማት መስኮች እመርታዎች እየታዩ እና እየተጨበጡ ሲሆን፣ ማንኛውም ሀገር ራሱን በራሱ ለማስቀጠል ማምረት ከሚገባቸው መሠረታዊ ነገሮች ቀዳሚ የሆነውን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ ትልቅ ሥራ ተሠርቷል። በተለይም በስንዴ ልማት እና በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብሮች የተረጅነትን ቀንበር ለመስበር እና ራሷን በራሷ ወደ መመገብ ከፍታ ለመድረስ ሀገራችን በፈጣን እርምጃ ላይ ትገኛለች።
ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢ ጥበቃ፣ በማዕድን ልማት እንዲሁም በአይሲቲ እና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፎች እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ መልኩ ለመበልጸግ ታላቅ ራዕይዋን እያሳካች መሆኗን በተጨባጭ ያሳያሉ።
ከሁሉም በላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት አኩሪ እመርታ የታየበት ሌላው የኢኮኖሚ ምሰሶ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ሲሆን፣ በተለይም የመከላከያ ኢንዱስትሪው ግንባታ ሀገራዊ ኩራት ሆኗል። ከዚህ ቀደም ለወታደሩ የሚሆን አልባሳት፣ ጫማ እና ተተኳሾችን ጭምር ከውጭ ታስገባ የነበረችው ኢትዮጵያ በዘመናዊ ሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ የተደራጀ ግዙፍ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ገንብታለች።
አሁን ላይ ከራሷ ፍጆታ አልፎ ለዓለም ገበያ በሚበቃ ደረጃ እያመረተች ሲሆን፣ ይህም ሀገራችን በቀላሉ ጥቃት የማይፈጸምባት እና የራሷን ደኅንነት በራሷ አቅም ያረጋገጠች ሉዓላዊት ሀገር መሆኗን በተግባር አሳይቷል።
በውስጥ አቅማችን የገነባነው ይህ ጥንካሬ በዲፕሎማሲው መስክም የኢትዮጵያን ገጽታ በመቀየር፣ ከእርዳታ ጠባቂነት አላቆ ወደ ታማኝ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ስትራቴጂካዊ አጋርነት አሸጋግሯታል። በዓለም አቀፍ መድረክ ያላት ተደማጭነትም ወደ ላቀ ምዕራፍ አድጓል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ አላት፤ የጀመረችውንም በአስተማማኝ ሁኔታ እየጨረሰች ነው። ሆኖም ሀገራችን ከዚህም በላይ የብልጽግና ጉዞዋን ከግብ ለማድረስ የበለጠ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ ስኬት ስለሚገባት እርካታ ሳይሆን መጠማት፣ በቃን ሳይሆን የበለጠ መፈለግ እና መሥራት ይገባናል" ብለዋል።
እንደ ሀገር ከተባበርን እና በአንድነት ከቆምን በፍጹም የማናልፋቸው ፈተናዎች፣ የማንሰብራቸው ተግዳሮቶች የሉም። የዛሬው ትጋታችን፣ የምናፈሰው ላብ እና የምንገነባው አቅም ለነገው ትውልድ የምናስረክበው ደማቅ ዐሻራችን ይሆናል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: