Search

የመስቀል በዓል፡ ከሃይማኖታዊ ትውፊት እስከ ኢኮኖሚ ምሰሶነት

እሑድ መስከረም 17, 2019 88

የመስቀል እና የደመራ በዓል ከ1 ሺህ 600 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በታላቅ መንፈሳዊ እና ባህላዊ ሥነ-ሥርዓት ሲከበር የቆየ ታላቅ ሕዝባዊ በዓል ነው።

በ4ኛው ክፍለ ዘመን በንግሥት እሌኒ መሪነት የክርስቶስ መስቀል የተቀበረበት ቦታ በጢስ ምልክት ተጠቁሞ መገኘቱን መሠረት በማድረግ፣ በየዓመቱ መስከረም 16 እና 17 ቀን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሪነት በታላቅ ድምቀት ይከበራል።

ይህ በዓል የክረምቱ ጨለማ አልፎ ዐደይ አበባ የሚያብብበትን እንዲሁም የብርሃን መተካትን የሚያበስር የተፈጥሮ እና የባህል ውህደት መግለጫ ጭምር ነው።

በኢትዮጵያውያን ዘንድ በዓሉ ያለው ተወዳጅነት ልዩ ሲሆን፣ ከሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓትነቱ ባሻገር ማኅበራዊ ውህደትን እና ሰላምን የሚያጠናክር ታላቅ መድረክ ነው።

በዓሉ ከመጀመሩ አስቀድሞ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ግላዊ እና የቡድን ቂሞች በሽማግሌዎች እና በሃይማኖት አባቶች አደራዳሪነት ይፈታሉ።

በተጨማሪም ደመራን የመሥራት፣ ዐደይ አበባን የመልቀም እና ባህላዊ ምግቦችን የማዘጋጀት ሂደት ከእናቶች እና አባቶች ወደ ልጆች የሚተላለፍበት ሕያው የዕውቀት ሽግግር ማዕከል ነው።

ከዚህም ባሻገር በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች፣ በተለይም በደቡቡ ክፍል በሚገኙ ማኅበረሰቦች ዘንድ በዓሉ የቤተሰብ መገናኛ እና የዓመቱ ታላቅ የደስታ ጊዜ ሆኖ በልዩ ድምቀት ይከበራል።

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በሚካሄደው ማዕከላዊ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ተወካዮች እና የውጭ ዲፕሎማቶች በአንድነት መሰብሰባቸው፣ ኢትዮጵያዊነት በባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ብዝኃነት ላይ የተገነባ የጋራ ማንነት መሆኑን በተግባር ያሳያል።

በታህሳስ ወር 2006 ዓ.ም በባኩ አዘርባጃን በተካሄደው ስብሰባ የመስቀል በዓል በዩኔስኮ 'የሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ዝርዝር' ውስጥ መመዝገቡ ትልቅ ታሪካዊ ክስተት ነበር።

ይህ ምዝገባ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ያስመዘገበችው የመጀመሪያው የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሲሆን፣ በዓሉን ዓለም አቀፍ የባህል ቱሪዝም መስህብ አድርጎታል።

ከምዝገባው በፊት በአብዛኛው በሀገር ውስጥ ምዕመናን ይጎበኝ የነበረው በዓል፣ ከምዝገባው በኋላ የቱሪዝም ካላንደር ዋነኛ መክፈቻ ሆኗል።

በዓሉ በኢኮኖሚው ዘርፍም ከፍተኛ መነቃቃትን ይፈጥራል። በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተጓዦች ወደ ትውልድ ቀዬአቸው በሚመለሱበት ወቅት ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር እና የሀብት ክፍፍል ይከናወናል።

በዚህም የሕዝብ ትራንስፖርት እንቅስቃሴ፣ የባህላዊ አልባሳት ሽያጭ፣ የሆቴል አገልግሎት፣ የአነስተኛ ንግድ እና የምግብ ዝግጅት ዘርፎች በከፍተኛ ደረጃ የገበያ ዕድገት ያሳያሉ።

የውጭ ቱሪስቶች ፍሰት መጨመርም የቱሪዝም ዘርፉን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማሳደግ በኩል ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

እንደ ሲኤንኤን፣ ቢቢሲ እና ናሽናል ጂኦግራፊክ ያሉ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በየዓመቱ በዓሉን መዘገባቸው፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን አዎንታዊ ገፅታ በማሻሻል የለስላሳ ኃይል (Soft Power) ተፅዕኖዋን አሳድጎታል።

ይህም ስኬት የሲዳማ ፊቼ ጫምባላላን፣ የኦሮሞ ገዳ ሥርዓትን፣ የጥምቀት በዓልን እና የሹዋልዒድ በዓልን በዩኔስኮ በተከታታይ ለማስመዝገብ ትልቅ ተቋማዊ ልምድ እና መነሳሳት ፈጥሯል።

የመስቀል በዓል ከማኅበራዊ እርቅ እስከ ብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ድረስ ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ተገንዝቦ፣ ይህን ውድ ቅርስ ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እና ለቱሪዝም ልማት በሚገባ መጠቀም የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: