የመስቀል በዓል ለኢትዮጵያውያን የአደይ አበባ እና የደማቅ ብርሃን እና የፌሽታ ቀን ብቻ አይደለም። ቀኑ የሙዚቃው ንጉሥ የክብር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ወደዚህች ዓለም የተቀላቀለበት ጭምር ነው።
መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም የተወለደው ጥላሁን በ68 ዓመቱ ሚያዝያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም በሞት ቢለየንም፣ ለሀገሩ ባበረከተው ታላቅ የኪነ ጥበብ አገልግሎት እስከዛሬም በሕዝቡ ልብ ውስጥ ሕያው ሆኖ አለ።
መስቀልን ጨምሮ በዓላት ሲከበሩ በየቦታው የጥላሁን የዓውዳመት ዜማዎች እንደሚያስተጋቡት ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በተደፈረ ቁጥርም የጥላሁን የሀገር ፍቅር ዜማዎች የወታደሩ የሞራል ስንቅ ሆነው አጀግነዋል።
ጥላሁን ገሠሠ የሀገር ፍቅርን በሙዚቃ መድረክ ላይ ብቻ አቀንቅኖ የሚያበቃ ድምፃዊ አልነበረም። የሀገር ሉዓላዊነት በተደፈረ ቁጥር ከጀግኖች ኢትዮጵያውያን ጋር እስከ ጦር ግንባር በመዝመት የሠራዊቱን ወታደራዊ ወኔ ሲቀሰቅስ የኖረ የኪነ ጥበብ አርበኛ ነው።
ኢትዮጵያ ሀገሬ፣ ሁሉም በሀገር ነው እና አጥንቴም ይከስከስ የሚሉት ዜማዎቹ የሀገርን ታላቅነት እና የአንድነትን አስፈላጊነት በኢትዮጵያውያን ሕሊና ውስጥ ያሰረጹ ድንቅ ሥራዎቹ ናቸው።
ሀገራዊ ጥሪ በተደረገባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ጥላሁን በአርበኝነት የተሞሉ ቀስቃሽ ዜማዎቹን ይዞ በጦር ሜዳዎች በመገኘት ወታደራዊ ወኔ እና ሥነ ልቦና ሲገነባ ቆይቷል።
የጥላሁን ገሠሠ የሙዚቃ ሥራዎች በግጥምና ዜማ ውህደታቸው ብቻ ሳይሆን፣ በውስጣቸው ባዘሉት ጥልቅ ሀገራዊ ራዕይ ዘመን አይሽሬ ሆነው ኖረዋል።
በሀገር ፍቅር፣ በሥራ ወዳድነት፣ በጽናት እና በእናትነት ዙሪያ የተጫወታቸው ዜማዎቹም ዛሬም ድረስ ለኢትዮጵያውያን የኪነ ጥበብ መመሪያ እና የመንፈስ ማደሻ ሆነው ያገለግላሉ።
የመስቀል በዓል ትውስታዎች ሲታደሱም፣ የጥላሁን ገሠሠ የልደት ታሪክ አብሮ ይነሳል።
የሙዚቃው ንጉሥ የክብር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ በሙያው ትውልድን በማንቃትና የሀገር ሉዓላዊነትን በማጽናት የማይደበዝዝ ዐሻራውን አኑሮ ያለፈ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: