Search

የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ጉዞ፡ ከጥንት የሥነ-ሕንፃ ጥበብ እስከ ዘመናዊ ዲጂታል ልዕልና

እሑድ መስከረም 17, 2019 61

የአሁኑ የኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞ በትውልድ ቅብብሎሽ የጸና፣ ከዘመናት በፊት ተነሥቶ ዛሬም ድረስ የዘለቀ ጥልቅ የፈጠራ ታሪክን መሠረት ያደረገ ነው።

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በራስ አቅም በመፍጠር እና በመተግበር ረገድ ፈር ቀዳጅ ነች። ዛሬ ላይ የምናየው የቴክኖሎጂ ተነሳሽነት ለኢትዮጵያውያን አዲስ ክስተት አይደለም።

ታሪክን መለስ ብለን ስንመረምር፣ ኢትዮጵያውያን ከዘመኑ ዓለም ጋር ለመራመድ ያደረጓቸው ጥረቶች አስገራሚ እና ደማቅ ምዕራፎች አሏቸው።

የአክሱም እና የየሓ መንግሥታት የነበሯቸው ጠንካራ የግንባታ እና የንግድ ጥበቦች የጥንቱን የኢትዮጵያ ከፍታ ዛሬም ይመሰክራሉ።

በዛግዌ ሥርወ መንግሥት በላሊበላ የተፈለፈሉ አስደናቂ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የኢትዮጵያውያንን የሥነ-ሕንፃ ጥበብ ልዕልና በጉልህ የሚያሳዩ ናቸው።

በ17ኛው ክፍለ ዘመን በጎንደር የተገነቡት ውብ አብያተ መንግሥታት፣ ድልድዮች እና የውኃ ማከፋፈያ መሠረተ ልማቶች በወቅቱ የነበረውን ከፍተኛ የከተማ ፕላን እና የድንጋይ ጥርብ ቴክኖሎጂን ያረጋግጣሉ።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን በዘመናዊ ዕውቀት ለማነፅ ታላቅ የቴክኖሎጂ ርምጃ ወስደዋል።

በደብረ ታቦር አቅራቢያ የሚገኘውን ጋፋት የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ ማዕከል በማድረግ "ሴባስቶፖል" የተሰኘውን መድፍ እስከማምረት ደርሰዋል።

ይህ ታሪካዊ ሙከራ የውጭ ጥገኛነትን በመስበር በራስ አቅም የመቆም የዘመናት ጽኑ ፍላጎታችንን የሚያሳይ የኢንዱስትሪ ሽግግር መሠረት ነበር።

በዚሁ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የቴሌኮም፣ የባቡር ሀዲድ፣ የኤሌክትሪክ እና የዘመናዊ ማተሚያ ቤት ቴክኖሎጂዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።

በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የጀመሩ እና ለዛሬ ጭምር የደረሱት የተቋማት ግንባታ ሥራዎች የኢትዮጵያውያንን ያልተቋረጠ በራስ የመቆም ጥረት ማሳያዎች ናቸው።

የአፍሪካ ሰማይ ላይ የነገሠው አየር መንገዳችን፣ በራሪ ነብሩ አየር ኃይላችን፣ ቴሌኮማችን እና ሌሎች ተቋማት ኢትዮጵያን ከዘመናት በፊት አልመው የተጀመሩ የልዕልና መገለጫዎች ናቸው።

ይህም ኢትዮጵያ የውጭ ፈጠራዎችን በዘፈቀደ የምትቀበል ሳትሆን፣ ከነባራዊ እውነታዋ ጋር አጣጥማ የመጠቀም ድፍረት የነበራት ቀዳሚ ሀገር መሆኗን ይመሰክራል።

የትላንትን እሴት ደምሮ፣ ዛሬን ለነገ የሚሠራው መደመር እነዚህን የፈጠራ እና የመሞከር ድፍረቶች ዛሬ ላይ በላቀ መልኩ አስቀጥሏል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ራዕይን መሠረት በማድረግ፣ ሀገራችን በከፍተኛ ቴክኖሎጂዎች መስክ አዲስ ታሪክ እየጻፈች ትገኛለች።

የትናንቱ የባቡር እና የስልክ መረብ ዝርጋታ ዛሬ ላይ ተሻሽሎ በሳተላይት፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ምርምሮች፣ እንዲሁም በግዙፍ የድሮን ቴክኖሎጂ ግንባታዎች ቀጥሏል።

ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያን ደማቅ ዐሻራ ያረፈበት እና ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ቀጣናውን እያስተሳሰረ የሚገኘውን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ጨምሮ፣ ዘመናዊ የኃይል ማመንጫዎችን በራስ አቅም በማልማት የኢነርጂ እና የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነቷን በተግባር አረጋግጣለች።

የትናንት መሪዎች የጀመሩት የቴክኖሎጂ ፍላጎት ዛሬ በሰለጠነ የትውልድ ዕውቀት እና ክህሎት ተደግፎ የሀገራችንን የብልጽግና ከፍታ እያሳለጠው ይገኛል።

ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ባለፈ አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር እና ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ ለመሰለፍ እርግጠኛ ሆና እየሠራች የምትገኘው።

ኢትዮጵያ ትናንትም ሆነ ዛሬ ለአዳዲስ ፈጠራዎች ያላት ዝግጁነት እና ፈጣን የመሞከር አቅም፣ የነገዋን የቴክኖሎጂ ልዕልና በጽናት እንድትመራ የሚያስችላት ታሪካዊ መገለጫዋ ነው።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: