Search

የኦሮሚያ ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን ወደ ተጨባጭ የለውጥ ሀይል ለማሸጋገር እንደሚሰራ አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ

ሰኞ መስከረም 18, 2019 134

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ዋነኛ ትኩረቱ እስካሁን የተጀመሩና የተገነቡ ፕሮጀክቶችን ወደ ተጨባጭ የለውጥ ሀይል በማሸጋገር ለህዝቡ የገባውን ቃል በተግባር ማዋል መሆኑን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት የክልሉን ያለፉት አምስት አመታት የልማት ክንውኖችና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ በጨፌ ኦሮሚያ 1ኛ ዓመት የ7ኛ የሥራ ዘመን የመጀመሪያ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ማብራሪያ ነው።

አቶ ሽመልስ በንግግራቸው የመንግስት ዋነኛና የመጨረሻ ግብ ህዝብን የሚያገለግል፣ አቅም የሚያጎለብትና ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ተቋም መገንባት መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በተለይም በገጠር ግብርና ምርታማነት፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝምና በከተሞች ዘመናዊነት ዙሪያ ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ዘርዝረዋል።

በእነዚህም የልማት ስራዎች የግብርናው ሽግግር ለአርሶ አደሩ፣ ለወጣቶችና ለሴቶች በሚጠቅም መልኩ የተቀመጠ ሲሆን፣ ተወዳዳሪ ትውልድ የሚፈጥር የትምህርት ስርአትና መከላከል ላይ ያተኮረ የጤና አገልግሎት ስርአት መዘርጋቱንም አብራርተዋል።

በተጨማሪም ባለሀብቶችን የሚያበረታቱ ህጎች መውጣታቸውንና ከተሞችን በማዘመን መንግስት አቅም ወደሚፈጠርበት ሁኔታ መሸጋገሩን ገልጸዋል።

ይህንን መሰረት በማድረግ ህዝቡ ሰላምን፣ ፍትህንና ብልጽግናን አጣምሮ በመጓዝ የተሻለ የህይወት ተስፋን እውን እንደሚያደርግ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታውቀዋል።

 

በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: